ህንድ ከኢራን ጋር ለምታደርገው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሶስተኛ ወገን ፈቃድ እንደማያስፈልግ ገለጸች

ህንድ ከኢራን ጋር ለምታደርገው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሶስተኛ ወገን ፈቃድ እንደማያስፈልግ ገለጸች፡፡

የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪ ሙራሌድሃራን ሀገራቸው ከኢራን ጋር ለምታደርገው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሶስተኛ ወገን ፈቃድ እንደማያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

ሚኒስትሩ በጽሁፍ ባስተላለፉት መልዕከታቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሌላ ሶስተኛ ሀገር ተጽህኖ ሊገደብ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡

በኢራን የነዳጅ ዘይት ግብይት ደንበኞች ላይ አሜሪካ ተጽእኖ እያሰደረች እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

ቀደም ሲል በኢራን ነዳጅ ምርት ላይ ማዕቀብ የጣለቸው አሜሪካ ህንድን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ከማዕቀቡ ጎን ለጎን እንዲገበያዩ የሰጠችው የ6 ወር የጊዜ ገደብ ባሳለፍነው የአውሮፓዊያኑ ግንቦት ወር ተጠናቋል፡፡

እስከ ፊታችን የአውሮፓዊኑ ህዳር 4፤ 2019 የኢራን የነዳጅ ምርት ግብይት ወደ ዜሮ ለማውረድ እየሰራች እንደሆነ ይነገራል፡፡

በዚህም ህንድ በሃይል ደህንነት፣ በንግድ ጉዳዮችና በኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቿ ዙሪያ ከቴህራን ጋር ለመምክር መዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡

በህንድ የኢራን አምባሳደር አሊ ቸገኒ ሀገራቸው ለህንድ አስተማማኝና ተመጣጣኝ ሃይል ማቅረብ እንደምትችል አስታውቀዋል፡፡

ኢራን በነዳጅ ምርት ግብይቱ ሂደት ምርቶችን በምርት የመቀያየር፣ የህንድ ሩጲ እና ሌሎች አማራጮችን እንደምትፈቅድም ተገልጿል፡፡

ህንድ ቻይናን ተከትላ ሁለተኛዋ የኢራን ነዳጅ ምርት ገዥ እንደሆነችም የፕሬስ ቲቪ ዘገባ ያመላክታል፡፡