ሩስያ ሚሳኤል ያለመገንባት ስምምነቱን እንድታድስ ኔቶ ጠየቀ

ሩስያ ሚሳኤል ያለመገንባት ስምምነትን የምታድስብት ጊዜ እየተገባደደ መሆኑን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሀፊ ጄንስ ስቶልንበርግ አስተወቁ።

ሩስያ ስምምነቱን ነሀሴ መባቻ ላይ ካላደሰች "የተጠና የመልስ ምት" ይሰጣል ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1987 አሜሪካና ሩስያ በአጭርና መካከለኛ ርቀት የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችን ላለመገንባት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩስያ ስምምነቱን በመጣሷ አሜሪካም 'ኢንተርሚድየት-ሬንጅ ኒውክሌር ፎርስስ' ወይም 'አይኤንኤፍ' በመባል የሚታወቀው ስምምነት የሚጥልባትን ግዴታ ከየካቲት ጀምሮ መወጣት እንደምታቆም ተናግረዋል።

ሩስያ ስምምነቱን እንዳልጣሰች ተናግራ ብዙም ሳይቆይ አዳዲስ የጦር መሣሪያ የማምረት እቅዷን ይፋ አድርጋለች።

ጄንስ ስቶልንበርግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ስምምነቱን የጣሱት የሩስያ ሚሳኤሎች፤ ኒውክሌር አዘል፣ ተንቀሳቃሽ፣ በቀላሉ ሊለዩ የማይችሉና በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ወደ አውሮፓ አገራት መድረስ የሚችሉ ናቸው።

"አይኤንኤፍ የጦር መሣሪያዎችን በመግታት በኩል ለዓመታት ያገለገለ ስምምነት ነው። አሁን ግን እያከተመለት መሆኑን እያየን ነው" ብለዋል።

ሩስያ ስምምነቱን ወደማክበር ልትመለስ እንደምትችል የሚጠቁም ነገር አለመኖሩን ገልጸው፤ "የ አይኤንኤፍ ስምምነት በሌለበትና ሩስያ በርካታ ሚሳኤሎች በምትገነባበት ዓለም ውስጥ ለመኖር እንገደዳለን" ብለዋል።

ጄንስ ስቶልንበርግ ሩስያ ስምምነቱን የምታድስበት ቀን ካለፈ በኋላ ኔቶ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ የተናገሩ ሲሆን፤ ይህም የአየር ሚሳኤል ዝግጅትና አዳዲስ የጦር መሣሪያ ቁጥጥርን ሊያካትት ይችላል።

ባለፈው ሳምንት ሩስያ ለኔቶ አባል አገሯ ቱርክ S-400 ሚሳኤሏን እንድታስረክብ መጠየቃቸው ይታወሳል።

አሜሪካ በምላሹ ቱርክን ከ ኤፍ-35 ተዋጊ ጀት ፕሮግራሟ እንደምታወጣ ተናግራ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንካራ ወደ ሞስኮ መቅረቧ በቱርክና በአሜሪካ መካከል ውጥረት መፍጠሩ ይታወቃል።

ቱርክ በኔቶ ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና ያወደሱት ዋና ጸሀፊው፣ ኔቶ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ተናግረዋል። "በሁለት ጠንካራ አባሎች መካከል ያለ አለመስማማት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው" ብለዋል።

የኔቶ አባል አገራት የመከላከያ በጀታቸውን ሁለት በመቶ ለማሳደግ እያደረጉ ያሉትን ጥረት ጄንስ ስቶልንበርግ አመስግነዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አባል አገራት አስተዋጽኦ እንዲያሳድጉ እየጠየቁ ነው።

ፕሬዘዳንቱ አባል አገራት የቻይናው የቴክኖሎጂ ተቋም ሁዋዊ ምርቶችን እንዳይጠቀሙ መጠየቃቸውም ይታወሳል። ዋና ጸሀፊው በበኩላቸው፤ መሰል ችግሮችን ለመፍታት አባል አገራት የሚስማሙበት ረቂቅ ስምምነት እየተረቀቀ መሆኑን ተናግረዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)