ኢራን “የ ሲ .አይ. ኤ ሰላይ ናቸው” ያለቻቸውን በሞት እቀጣለሁ አለች

ኢራን ለሲአይኤ እየሠሩ ነበር ያለቻቸውን 17 ሰላዮች በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ይፋ አደረገች። ከነዚህ ገሚሱ ሞት ተፈርዶባቸዋል ተብሏል።

የኢራን የደህንነት ሚንስትር እንዳለው፤ ተጠርጣሪዎቹ ስለ ኒውክሌር፣ መከላከያ እና ሌሎችም ዘርፎች መረጃ እየሰበሰቡ ነበር።

የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ክስ "ሀሰት ነው" ሲሉ አጣጥለዋል። በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ሳቢያ ሁለቱ አገራት እንደተፋጠጡ ነው።

ትራምፕ ከዓለም አቀፉ የኒውክሌር ስምምነት ባለፈው ዓመት ወጥተው ኢራን ላይ የንግድ ማእቀብ መጣላቸው ይታወሳል።

ኢራን እስሩን እንዳሳወቀች "ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተቸገርኩ ነው" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ኢራን ለአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ይሰራሉ ያለቻቸውን ግለሰቦች ያሠረችው ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ተናግራለች።

17ቱም ኢራናዊ ሲሆኑ፣ በመከላከያና ኒውክሌር ማዕከሎች አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አንድ የኢራን ከፍተኛ የደህንነት ኃላፊ ገልጸዋል። ከታሠሩት መካከል ምን ያህሉ ሞት እንደተፈረደባቸው ያሉት ነገር የለም።

የኢራን የደህንነት ሚኒስትር መሀሙድ አልቪ "ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰላዮችን እሥር የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም በኢራን ቴሌቭዥን ይታያል" ብለዋል።

የደህንነት ተቋሙ የዘጋቢ ፊልሙን ቅንጫቢ የያዘ ሲዲ ለቋል። በሲዲው የሰላዮች ስብሰባና ቃለ ምልልስን በማስመሰል የተሠራ ትዕይንትም ይታያል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ሳለ በሲአይኤ የተመለመሉ ይገኙበታል። አንዳንዶቹ ደግሞ የአሜሪካ ቪዛቸውን ለማሳደስ ሲሞክሩ ሲአይኤ ተጽዕኖ አድርጎ የመለመላቸው ናቸው ብለዋል። የተቀሩት በገንዘብ፣ በህክምና አገልግሎትና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞች ተደልለዋል ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ወር ኢራን ከ "ሲአይኤ የስለላ ሰንሰለት ጋር የተገናኘ" ነው ያለችውን መስመር መበጣጠሷን አሳውቃ ነበር። የአሁኑ ከዚህ ሰንሰለት ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።

የአካባቢውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች የኢራን መግለጫን በጥርጣሬ ተመልክተውታል።

የኢራን ደህንነት ሚኒስትር ባለፈው ወር የሲ አይ ኤን የስለላ ሰንሰለት በጣጥሻለሁ ብትልም፤ አሁን ደግሞ 17 ተጠርጣሪዎችን አሥሬያለሁ ብላለች።

አንዳንዶች እንደሚሉት 17ቱ ግለሰቦች ለበርካታ ዓመታት በስለላ የተጠረጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ኢራን ውስጥ ለተለያዩ አገራት ሲሰልሉ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ብዙ እስረኞች አሉ።

የኢራን የደህንነት ሚንስትር መግለጫ ያወጣው አዳዲስ ተጠርጣሪዎች አሥሮ ሳይሆን፤ ከሪቮሉሽነሪ ጋርዶች ጋር እየተደረገ ያለውን ፉክክር አስታክኮ ነው የሚሉም አሉ።

ከሁለት ሳምንት በፊት የኢራን ቴሌቭዥን የኢራንን የደህንነት ተቋም የሚያሞግስ ዘጋቢ ፊልም አቅርቦ ነበር። አሁን ደግሞ የደህንነት ሚኒስትሩ ስኬቱን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ሊያቀርብ ነው።

በኢራን ውስጥ ያሉት ተፎካካሪ ተቋሞች አንዳቸው ከሌላቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረትም ይመስላል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)