የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አሜሪካዊያን ጥላቻና ዘረኝነት የሚሰብኩ መሪዎቻቸውን እንዲያወግዙ ጥሪ አቀረቡ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አሜሪካዊያን ጥላቻና ዘረኝነት የሚሰብኩ መሪዎቻቸውን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንም እንኳ ኦባማ ይህ ነው ያ ነው ብለው ስም ባይጠቅሱም አስተያየታቸው በተከታታይ ቀናት ከተከሰቱ የጅምላ ግድያዎች በኋላ መምጣቱ ትችቱ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አይቀርም አስብሏል።

ቴክሳስ ኦሃዮ ውስጥ 31 ሰዎች በጅምላ ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ጥላቻ እና የነጭ የበላይነትን ማስወገድ አለብን ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ኦባማ ሥልጣን ላይ የጦር መሣሪያ ግዥ ቁጥጥር እንዲደረግበት ቢታገሉም ሳይሳካላቸው መቅረቱ አይዘነጋም። በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2015 ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የጦር መሣሪያ ላይ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ሕግ ማፅደቅ አለመቻላቸው እንደሚከነክናቸው ገልፀው ነበር።

ኦባማ፤ ትራምፕ ስደተኞችን አስመልክቶ ስላሰሟቸው አጨቃጫቂ ንግግሮች ምንም ዓይነት አስተያየት ለመስጠት ቢቆጠቡም ሰኞ ዕለት በለቀቁት መግለጫ 'ጥላቻን የሚሰብኩ መሪዎችን እናውግዝ' ብለዋል።

«ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ፍራቻን የሚነዙ፣ ዘረኝነት የሚያበረታቱ፣ እነሱን የማይመስሉ ሰዎችን [ስደተኞችን ጨምሮ] የሚያገሉ፣ አሜሪካ ለተወሰኑ ዓይነት ሰዎች ብቻ ነች የሚሉ መሪዎችን አምርረን ማውገዝ አለብን።» በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት የሜክሲኮ ዜጎች ደፋሪዎች እና ገዳዮች ናቸው ማለታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ከሁለት ተከታታይ የጅምላ ጥቃቶች በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ "የአዕምሮ ጤና እና የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕጉ ላይ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ፤ የጅምላ ጥቃት አድራሾች ከበድ ያለ ቅጣት ያስፈልጋቸዋል" የሚል መግለጫ አውጥተዋል።

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ያቀረበውን የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሕግ ይደግፉ አይደግፉ ግን ያሉት ነገር የለም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)