ቻይና እና ሩሲያ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በአሜሪካ ሚሳኤል ሙከራ ዙሪያ ስብሰባ እንዲጠራ ጠየቁ

ቻይና እና ሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት በአሜሪካ ሚሳኤል ሙከራ ዙሪያ ስብሰባ እንዲጠራ መጠየቃቸው ተገለጸ፡፡
አሜሪካ ባሳላፍነው ሰኞ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎችን የማልማትና የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት መግለጫ መስጠቷ ይታወሳል፡፡
ቤጅንግ እና ሞስኮ ጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ሰላምና መረጋጋት ስጋት በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዲመክር ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
በሳለፍነው ሰኞ የአሜሪካ መከላከያ በሰጠው መግለጫ የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤል ሙከራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ሙከራው ከ500 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ኢላማውን መምታት መቻሉም ነው በመግለጫው የተመላከተው፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ማርክ ኢስፐር ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስም የሚሳኤል ሙከራው ለቻይና እና ሩሲያ ብሎም ለሰሜን ኮሪያ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
አሜሪካ በቀዝቃዛው ጦርነት ከተፈራረመችው የመካከለኛው ርቀት ሚሳኤል መጠቀም ከሚከለክለው ስምምነት መውጣቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ሙከራው የመጀመሪያው መሆኑምን ዘገባው ያስረዳል፡፡ (ምንጭ፡-አልጀዚራ)