ቻይና የአሜሪካ የጦር መርከብ የወደብ ጉብኝት ጥያቄን ውድቅ አደረገች

የአሜሪካ ባህር ኃይል ንብረት የሆነው የጦር መርከብ  ኪንግዳኦ የተሰኘችውን የቻይና የወደብ ከተማ ለመጎብኘት ያቀረበው ጥያቄ በቻይና ውድቅ ተደርጓል፡፡

እንደ አሜሪካ መከላከያ ባለስልጣናት ከሆነ ሀገሪቱ በወር ለሁለተኛ ጊዜ ነው የጉብኝት ጥያቄውን ውድቅ ያደረገችው፡፡

ከዚህ በፊት ሁለት የአሜሪካ ባህር ኃይል መርከቦች ወደ ሆንግ ኮንግ ለማቅናት አቅርበውት የነበረውን ጥያቄ ቻይና ሳትቀበለው መቅረቷን የአልጀዚራ ዘገባ አስታውሷል፡፡

ይህን ተከትሎ በንግድ ጦርነት የሚታወቀው የሁለቱ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ፍጥጫ  መልኩን ቀይሮ ወደለየለት ግጭት እንዳያመራ ስጋትን ከደቀነም ዋል አደር ብሏል፡፡

በተጨማሪም አሜሪካ በታይዋን ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብነትም  በቻይና እና አሜሪካ መካከል እሰጥ አገባው እንዲካረር አድርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ  ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከቻይና ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ማስታወቃቸው ውጥረቱ እንዳይባበስ ይረዳል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል፡፡