ቻይና ከ8 ሺህ በላይ አዳዲስ ወታደሮችን ወደ ሆንግኮንግ መላኳ ተገለጸ

ቻይና ከስምንት ሺህ እስከ 10 ሺህ የሚገመት አዳዲስ ወታደሮቿን ወደ ሆንግኮንግ መላኳ ተገልጿል፡፡

አዳዲሶቹ ወታደሮች የተላኩት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ነው ተብሏል፡፡

ሆንግ ኮንግ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ተላቃ ለቻይና ከተመለሰች ሃያኛ ዓመት ብታስቆጥርም የምትተዳደረው ግን በ«አንድ ሃገር፤ ሁለት ሥርዓቶች» ፖሊሲ ነው፡፡

የኋላ ኋላ ግዛቲቱ ሙሉ በሙሉ ለቻይና ተላልፋ ተሰጥታ በቻይና እንድትተዳደር ውሳኔ ከተሰጠ ሀኋላ ግን አደባባዮቿ በመንግስት ተቃዋሚዎች ተሞልተው ወራትን አስቆጥረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከፖሊሶች ጋር ግጭቶች መፈጠራቸው ይታወሳል፡፡ የግዛቲቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የተቃውሞ ስልፍም 1,000 የሚጠጉ የአውሮፕላን በረራዎች ተሰርዘው ነበር።

የሆንግኮንግ ተቃውሞ መጠኑ እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎም ቻይና ከስምንት ሺህ እስከ አስር ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ሰራዊቶችን ዛሬ ከሰዓታት በፊት ወደ ሆንግ ኮንግ መላኳን አልጀዚራ ሮይተርስን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ቻይና ሆንግኮንግ ውጥረት እየተባባሰ ሲመጣ ቁጭ ብየ አልመለከትም ማለቷን የዘገበው አልጀዚራ ባለፈው ዓመት ሃገሪቱ የወታደሮቿን ቁጥር እንዳልጨመረች ይፋ ማድረጓን ጠቁሟል፡፡

ቻይና ዛሬ ባወጣችው መግለጫ ደግሞ የወታደሮቿን ቁጥር ይበልጥ ልትጨምር እንደምትችል የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡