ኢራን ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ወደ ኒውክሌር ስምምነቱ ልትመለስ እንደምትችል አስታወቀች

ኢራን ከአምስቱ ሃያላን ሀገራት ጋር ወደ ገባችው የኒውክሌር ስምምነት ልትመለስ እንደምትችል የሀገሪቱ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራቅጭ ኢራን በፈረንጆቹ 2015 ለገባችው የኒውክሌር ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተገዥ ልትሆን እንደምትችል አረጋግጠዋል።

ይህን ለማድረግ ግን ቴህራን በቀጣዮቹ አራት ወራት 15 ቢሊየን ዶላር ከነዳጅ ሽያጭ አልያም በብድር መልክ ማግኘት እንዳለባት የፋርስ ዜና አገልግሎትን ዋቢ አድርጎ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

አባስ አራቅጭ አንድም የአውሮፓ ሀገራት ከኢራን የነዳጅ ዘይት መግዛት ይኖርባቸዋል አልያም በአራት ወራት ውስጥ ከሽያጭ ልታገኝ የሚገባውን ገንዘብ በፈለገችው ጊዜ ልትጠቀመው በምትችልና ረዘም ባለ ጊዜ በሚመለስ የብድር አይነት ሊፈቅዱላት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ሀገራቸው ለስምምነቱ ተገዥ እንደማትሆን ተናግረዋል፡፡

ፈረንሳይ በበኩሏ ኢራን ለስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተገዥ መሆን ከቻለች ለቴህራን እስከ መጭው ገና መጨረሻ ድረስ በፈለገችው ጊዜ ልትጠቀመው የምትችለው 15 ቢሊየን ፓውንድ በብድር መልክ መስጠት የሚያስችል ረቂቅ አቅርባለች።

ረቂቁ ስምምነቱን ለመታደግ ያግዛል ቢባልም እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልተስተዋለም።

አሜሪካ ከኒውክሌር ስምምነቱ ባለፈው አመት ከወጣች እና በቴህራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ከጣለች በኋላ ኢራን ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘው ገንዘብ አሽቆልቁሏል።

የ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይና ጀርመን በተጨማሪነት ከኢራን ጋር የገቡት ስምምነት ነው። (ምንጭ፡-ሬውተርስ)