የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር  እስራኤል ኋይት ኃውስን ትሰልላለች የሚለውን ዘገባ አስተባበሉ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፤ አገራቸው አሜሪካን ትሰልላለች ተብሎ የወጣውን ዘገባ አስተባብለዋል።

እስራኤልን አሜሪካን በመሰለል የሚወነጅለው ዘገባ በአሜሪካ በሚገኝ 'ፖለቲኮ' በተሰኘ የዜና ድረ ገፅ ላይ የወጣው ሐሙስ ዕለት ነበር።

'ፖለቲኮ' የተሰኘው ይህ የዜና ድረ ገፅ፤ ሦስት የቀድሞ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጠቅሶ፤ ዋይት ኃውስ አቅራቢያ ተገኘ ካለው የመከታተያ መሣሪያ ጀርባ እስራኤል ትኖርበታለች ሲል ዘግቧል።

ነገር ግን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቢሮ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው ውንጀላው ነጭ ውሸት ነው።

በአሜሪካ በየትኛውም የስለላ ተግባር ላለመሳተፍ ረዥም ጊዜ ፀንቶ የቆየ መግባባት አሠራር አለ ይላል መግለጫው ።

ሐሙስ ዕለት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዜጠኞች ስለ ሪፖርቱ ሲጠየቁ፤ እስራኤል አሜሪካን ትሰልላለች ብለው እንደማያምኑ ተናግረው ነበር።

እጅጉን ለማመን ተቸግሬያለሁ፤ ከእስራኤል ጋር ያለኝ ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር ያለው የኒውክሌር ስምምነት ማብቃቱንና አሜሪካ በእስራኤል የሚገኘውን ኢምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ለማዞር የወሰነችበትን አወዛጋቢ ውሳኔ በአስረጅነት ጠቅሰዋል።

ይህንን ወሬ አላምነውም፤ አይሆንም ማለት ፤ ግን አልችልም ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ