አሜሪካ ሳዑዲ ላይ የተቃጡት ጥቃቶች መነሻቸው ከኢራን መሆናቸውን ገለጸች

አሜሪካ ሳዑዲ ላይ የተቃጡት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መነሻቸው ከኢራን ስለመሆኑ ደርሼበታለው ማለቷ ተገለጸ፡፡

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማትን ዒላማ አድርገው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ጥቃቶች መነሻቸው ከደቡባዊ ኢራን ነው።

ኢራን በበኩሏ ከጥቃቶቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ስትል ቆይታለች።

በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን በሳዑዲ ጥቃቱን ያደረስነው እኛ ነን ቢሉም ሰሚ አላገኙም።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢኔርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው'' ለማለት ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።

ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት፤ ጥቃቱ የተሰነዘረበት አቅጣጫ እና ስፋት ከግምት ውስጥ ሲገባ የሁቲ አማጽያን ፈጽመውታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።

የሁቲ አማጽያን ከዚህ ቀደም ወደ ሳዑዲ የድሮን ጥቃቶችን አድርሰዋል፤ ሚሳዔሎችንም አስወንጭፈዋል። የአሜሪካ ባለስልጣናት ይህን ጥቃት ግን የሁቲ አማጽያን መፈጸም የሚያስችል ቁመና የላቸውም፤ እንዲሁም ጥቃቶቹ የተሰነዘሩት በየመን የሁቲ አማጽያን ከሚቆጣጠሩት ስፍራም አይደለም።

በሳዑዲ ላይ ጥቃቱ ከተሰነዘረ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጨማሪ ማሳየቱ ይታወሳል።

የሳዑዲ አረቢያ ኢነርጂ ሚኒስትር ትናንት በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ተጠግነው ወደ ቀደመ የማምረት አቅማቸው በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ይመለሳሉ ብለዋል።