ቬንዙዌላ ቀንደኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪን ፈታች

ቬንዙዌላ ቀንደኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትን ኤድጋር ዛምብራኖን ከእስር መፍታቷን አስታውቃለች፡፡

ኤድጋር ከሌላው የተቃዋሚ መሪ ሁዓን ጉአይዶ ጋር በመሆን  የቬንዙዌላ መንግስትን ለመገልበጥ ወታደራዊ አመፅን ቀስቅሰዋል በሚል ላለፉት አራት ወራት በእስር ቆይተዋል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ታሬክ ዊሊያም ሳዓብ ከብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር በተወሰኑ ነጥቦች ዙሪያ ከስምምነት መደረሱን ተከትሎ መንግስት ግለሰቡ እንዲፈቱ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የኤድጋር ዛምብራኖን የክስ መዝገብ አለመዘጋቱንና ከሀገር እንዳይወጡ የተቀመጠው ክልከላ አለመነሳቱን ነው የቢቢሲ ዘገባ ያመለከተው፡፡

ዛምብራኖ መፈታቱን ተከትሎ ከእርሱ ጋር የነበሩ አራት ጓደኞቹን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

ሁዓን ጉአይዶ በበኩሉ የዛምብራኖ ከእስር መፈታት የአለምአቀፉ ማህበረሰብ የፈጠረው ጫና ውጤት እንደሆነ በትዊተር ገፁ አስፍሯል፡፡

እ.አ.አ በ2018 ወርሃ ግንቦት በቬንዝዌላ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተዓማኒነት የጎደለው ነው የሚል ዘመቻ መጀመሩን ተከትሎ ሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታ ቆይታለች፡፡
 

ምንጭ፦ አልጀዚራ