ጥቅም ላይ የዋሉት መሣሪዎች ኢራን ተጠያቂ መሆኗን ያረጋግጣሉ- ሳዑዲ

በአገሪቱ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ በደረሰው ጥቃት ጥቅም ላይ የዋሉት መሣሪዎች ኢራን ተጠያቂ መሆኗን ያረጋግጣሉ ስትል ሳዑዲ ገለጸች፡፡

የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስትር፤ በአገሪቱ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ከደረሰው ጥቃት የተሰበሰቡ ናቸው ያላቸውን የድሮን እና የሚሳዔል ስብርባሪዎች አሳይተዋል።

መከላከያ ሚኒስተሩ ስብርባሪዎቹ ጥቃቱን ያደረሰችው ኢራን ስለመሆኗ ማሳያ ናቸው ብሏል።

"18 ድሮኖች እና ሰባት ሚሳዔሎች ወደ ሳዑዲ ተተኩሰዋል" ያለው የሳዑዲ መከላከያ፤ የጥቃቶቹ መነሻ የመን አይደለችም ብሏል።

በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው እና በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማጽያን "ጥቃቱን ያደርስነው እኛ ነን" ቢሉም ሰሚ አላገኙም።

ሳዑዲ ላይ ለተቃጣው ጥቃት፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢራንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር። ኢራን በበኩሏ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ እጇ እንደሌለባት በተደጋጋሚ ስትከራከር ቆይታለች።

የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማትን ዒላማ አድርገው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ጥቃቶች መነሻቸው ከደቡባዊ ኢራን ነው በማለት የሳተላይት ምስሎችን እንደማሳያ አድርገው አቅርበው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ የሳዑዲን ነዳጅ ማቀነባበሪያ ለመምታት ጥቅም ላይ የዋሉት የድሮን እና የሚሳዔል አይነቶችን ለይተናል ብለዋል።

''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም'' ብለው የነበሩት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ፤ ትናንት ሳዑዲ አረቢያ ከደረሱ በኋላ ሁኔታውን "የጦርነት ትንኮሳ" ሲሉ ገልጸውታል።

የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮለኔል ቱርኪ አል-ማልለኪ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው "በኢራን ድጋፍ ሰጪነት ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረው እንደተናገሩት፤ በትክክል ድሮን እና ሚሳዔሎች ጥቃት ከየት እንደተሰነዘሩ ለማወቅ እየሠራን ነው ብለዋል።

ጥቃቱን ለመሰንዘር ጥቅም ላይ ከዋሉት የጦር መሣሪያ ስብርባሪዎች በተገኘው መረጃ መሰረት፤ ቢያንስ አንዱ መሣሪያ የኢራን ጦር የሚጠቀምበት ነው ተብሏል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)