አሜሪካ ጦሯን ወደ ሳዑዲ ልትልክ መሆኑን አስታወቀች

አሜሪካ በሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ወታደሮቿን ልትልክ መሆኑን አስታወቀች።

የመከላከያ ሚኒስቴር ፀሐፊ የሆኑት ማርክ ኤስፐር፤ በሳዑዲ የሚሰማራው ጦር "መከላከል ላይ ያተኮረ" ተልዕኮ ሊሰጠው እንደሚችል ለጋዜጠኞች ጠቁመዋል። ምን ያህል ወታደር እንደሚሰማራ ግን ያሉት ነገር የለም።

በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቱ አማፂያን ባለፈው ሳምንት በሳዑዲ ሁለት የነዳጅ ማቀነባበሪያ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን እንወስዳለን ብለዋል። ሆኖም አሜሪካም ሆነች ሳዑዲ አረቢያ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት ኢራንን ነው።

አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ወታደራዊ እሰጥ አገባ ውስጥ ላለመግባት በሚል "ከፍተኛ የሆነ" ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል ተናግረው እንደነበር የሚታወስ ነው።

አዲሱ ማዕቀብ የሚያነጣጥረው የኢራን ማዕከላዊ ባንክንና ሉዓላዊ የሀብት ፈንድን መሆኑን ትራምፕ ተናግረዋል።

ሚስተር ኤስፐር መግለጫ የሰጡት የጥምር ጦሩ የበላይ ኃላፊ ከሆኑት ጄነራል ጆሴፍ ደንፎርድ ጁኒየር ጋር ነው።

ሳዑዲ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስን ድጋፍ ጠይቀዋል ብለዋል ሚስተር ኤስፐር። የሚላከው ኃይል የአየርና የሚሳኤል መከላከል አቅምን ከፍ ያደርጋል ተብሎ የታቀደ ሲሆን፤ አሜሪካ ደግሞ ለሁለቱ አገራት "ወታደራዊ ቁሳቁስን ማቅረቡን ታፋጥናለች" ብለዋል።

ጄነራል ደንፎርድ የወታደራዊ ስምሪቱን "የተለሳለሰ" ያሉ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠር እንዳልሆነም አስታውቀዋል። ከዚህ ውጪ ግን ምን ዓይነት ጦር እንደሚሰማራ ፍንጭ አልሰጡም።

እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ከሆነ፤ ጋዜጠኞች ሚስተር ኤስፐርን ኢራን ላይ የአየር ድብደባ ለማካሄድ ታቅዶ እንደሆነ ሲጠየቁ "በአሁኑ ሰዓት እዚያ ውሳኔ ላይ አልደረስንም" ማለታቸውን ዘግቧል።

የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስትር፤ በአገሪቱ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ከደረሰው ጥቃት የተሰበሰቡ ናቸው ያላቸውን የድሮን እና የሚሳዔል ስብርባሪዎች በማሳየት "ጥቃቱን ያደረሰችው ኢራን ነች" ሲል ከስሷል።

"18 ድሮኖች እና ሰባት ሚሳዔሎች ወደ ሳዑዲ ተተኩሰዋል" ያለው የሳዑዲ መከላከያ፤ የጥቃቶቹ መነሻ የመን አይደለችም ሲል አስረግጦ ይናገራል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)