በሳዑዲ ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ገለጹ

በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ ሁለት የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ውጥረት አስመልክተው ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ በቅርቡ በሳዑዲ ዓረቢያ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በኢራን የተወሰደ እርምጃ መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ አለመቅረቡን አንስተዋል።

በመሆኑም ተጨባጭና ተዓማኒ መረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ ኢራንን ብቻ ለጥቃቱ ተጠያቂ ማድረግ ውጤቱ የከፋ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

በአንፃሩ ጥቃቱ የተፈጸመው ከተለያዩ የየመን አካባቢዎች በመጡ የሁቲ አማጽያን አማካኝነት መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ተናግረው፤ ቡድኑ ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ መሆኑ መረጃውን ይበልጥ ተዓማኒ ያደርገዋል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ያለምንም ተጨባጭ መረጃ በድርጊቱ ኢራንን የሚወነጅሉበት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለውና የቀጠናውን ሰላም ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተያዘው ወር መጀመሪያ አካባቢ በሳዑዲ ሁለት የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማት ላይ በድሮን የታገዘ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ለጥቃቱ ኢራንን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በየመን በስፋት የሚንቀሳቀሱትና በኢራን መንግስት የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን ለጥቃቱ ሃላፊነት ወስደዋል።

ኢራን በበኩሏ በጥቃቱ እጇ የሌለበት መሆኑን በመግለፅ ጉዳዩን አስመልክቶ ሊፈጸምባት የሚችልን ማንኛውም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆኗን ማስታወቋ የኒታወስ ነው ሲል ሬውተርስ ዘግቧል፡፡