ቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ የተመሰረተበትን 70ኛ አመት እያከበረች ነው

ቻይና- የቻይና ህዝቦች ሪፐብሊክ (ፒአርሲ) ተብሎ የሚጠራውን የኮሚዩኒስት ፓርቲ የተመሰረተበትን ሰባኛ አመት በደመቀ ሁኔታ እያከበረች ነው።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1949 ማኦ ዜዱንግ ወይም ሊቀመንበር ማኦ የኮሚዩኒስት ጥምር ኃይሎች ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ማሸነፋቸውን ተከትሎ ፒአርሲ መመስረቱን አወጁ።

ዘመናዊት ቻይና በሚያስገርም ፍጥነት እያደገች ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ ነፃነትን በመግታትም የሰላ ትችት ይቀርብባታል።

ፕሬዚዳንት ዢ ሺንፒንግ በቲናንማን አደባባይ የተደረገውን ከፍተኛ ወታደራዊ ትዕይንትን ተከትሎ እንደተናገሩት የትኛውም ኃይል ቻይናን እንደማያነቃንቃት ነው።

"የትኛውም ኃይል ቢሆን ቻይናንም ሆነ ህዝቦቿን ወደፊት ከመሄድ አያግዳቸውም" በማለት ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ማኦ የቻይና ህዝቦች ሪፐብሊክን መመስረት ባወጁበት ተመሳሳይ ቦታ ከመቆም በተጨማሪ ማኦ በጊዜው ለብሰውት የነበረውን ተመሳሳይ ልብስም ለብሰው ታይተዋል ነው የተባለው።

ፕሬዚንዳት ዢ አብዮታዊውንና መስራቹን አባትም ራዕይም ሆነ ትዝታ ከማጋራትም አልተቆጠቡም፡፡ ነገር ግን በዛሬው ዕለት የሚደረገውን አከባባበር በሆንግ ኮንግ የሚደረገው ተቃውሞ እንዳያጠለሸው ተሰግቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ቤጂንግ በሆንግ ኮንግ ማህበረሰብና ፖለቲካ ላይ የምታደርገውን ቅጥ አልባ ቁጥጥር በመቃወም ተቃውሟቸውን ማሰማት ከጀመሩ ዋል አደር ያሉ ሲሆን፤ በዛሬውም ዕለት ተቃውሟቸውን ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የመከላከያ ሚኒስትር እንዳሳወቀው፤ 15ሺ ወታደሮች፣ 580 ወታደራዊ ቁሶች እንዲሁም 160 የጦር አውሮፕላኖች በዚህ ወታደራዊ ትዕይንት ተሳታፊ ሆነዋል።

የሀገሪቷ አዲስ ወታደራዊ የቴክኖሎጂ ግኝቶች በትእይንቱ ላይ የቀረቡ ሲሆን፤ ታንኮች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ዲኤፍ 41 የሚል መጠሪያ የተሰጠው የባሊስቲክ ሚሳይልም ይገኙበታል።

ከወታደራዊ ትዕይንቱ በተጨማሪ ከተለያየ የማህበረሰቡ ክፍል የተውጣጡ ከመቶ ሺ በላይ ግለሰቦች የሚሳተፉበት ደመቅ ያለ ዝግጅትም የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም አርሶ አደሮች፣ መምህራን፣ ዶክተሮችና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዝግጀቱ ለመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ለተጋበዙ ግለሰቦችና ለውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች ክፍት ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች በያሉበት ሆነው የሚከታተሉት ይሆናል።

የፀጥታው ቁጥጥር በማዕከላዊ ቤጂንግ ለሳምንታት ያህል በጣም የጠበቀ ሲሆን፣ በተለይም በትዕይንቱ አካባቢ ድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላንን) ጨምሮ ለውድድር የሚሆኑ እርግቦችም ተከልክሏል።

ሚዲያን ሳንሱር በማድረግ በምትተቸው ቻይና ወታደራዊ ትዕይንቱን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥጥር የጠበቀ ሲሆን፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች የፕሮግራሞች ዝርዝር የተሰጣቸው ሲሆን በኦንላይንም ላይ የኮሚዩኒስት ፖርቲንም ሆነ መሪዎቹን መተቸት ክልክል ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)