የተባበሩት መንግሥታት ብዙዎችን እየቀጠፈ ያለውን የኢራቅ ተቃውሞ እንዲቆም ጠየቀ

የተባበሩት መንግሥታት ብዙዎችን እየቀጠፈ ያለውን የኢራቅ ተቃውሞ እንዲቆም ጠየቀ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት "ትርጉም አልባ ሞት" ባለው የኢራቅ ተቃውሞ የሟቾች ቁጥር መቶ ደርሷል።

ተቃዋሚዎቹ ሥራ አጥነት፣ ያልተሟሉ የሕዝብ አገልግሎቶችና በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስናን ለመቃወም የወጡ መሆናቸው ተነግሯል።

በኢራቅ የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ተልዕኮ ዋና ኃላፊ ጂኒ ሄኒስ ፕላስቻርት "አምስት ቀናት ሙሉ ሞትና ጉዳት ተከስቷል፤ ይህ ሊቆም ይገባል" ብለዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦች ችሎት ፊት ሊቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቅዳሜ መስከረም 24፣ 2012 የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ቁጥር የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ በምስራቃዊ ባግዳድ በትነዋል።

ይህንንም ተከትሎ በመዲናዋ ባግዳድ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ የፀጥታ ኃይሎች የጎማ ጥይቶችን እንዲሁም አስለቃሽ ጋዞችን ተጠቅመዋል ተብሏል።

የኢራቅ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ምክር ቤት እንዳሳወቀው፤ ቢያንስ 99 ሰዎች እንደሞቱና አራት ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች ደግሞ ተቃውሞ ከጀመረበት ማክሰኞ እለት ጀምሮ እንደቆሰሉ ነው። ተቃውሞው ከመዲናዋ ወደ ደቡባዊ ኢራቅም ተዛምቷል።

የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ የተባለው ይህ አለመረጋጋት ከሁለት ዓመት በፊት አይኤስ ተሸንፏል መባሉ ከታወጀ በኋላ ካጋጠመው የከፋ ነው ተብሏል።

እየተፍረከረከ ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብደል ማሃዲን መንግሥትንም የፈተነ ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ዓመት ሆኗቸዋል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት የሰዓት እላፊ በማወጅ እንዲሁም ኢንተርኔትን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ተቃውሞውን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡።