በአሜሪካዊቷ ፖሊስ አምበር ጉይገር የፍርድ ሂደት ምስክርነት የሰጠው የዐይን እማኝ ተገደለ

አሜሪካዊቷ ፖሊስ አምበር ጉይገር በዳላስ ቴክሳስ ውስጥ ነዋሪ ስትሆን፤ ቦታም ጂን የተባለ ግለሰብን አፓርትመንቱ ውስጥ በጥይት ተኩሳ በመግደል ከሰሞኑም ተፈርዶባታል።

በግድያው ላይ የዐይን እማኝ ሆኖ ቀርቦ ምስክርነት የሰጠውም ጆሹዋ ብራውን በተተኮሰበት ጥይት ሞቷል።

ፖሊሷ የራሷ አፓርትመንት መስሏት ስትገባ ጂን ሶፋ ላይ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን ቤቷን ሰብሮ የገባ መስሏት ያለምንም ጥያቄ ሁለት ጊዜ በጥይት ተኩሳ ገድለዋለች።

ግለሰቡ ከካሪቢያን ደሴቶች አንዷ ከሆነችው ሴንት ሉሺያ የመጣ ሲሆን በሒሳብ ሠራተኝነት ይሠራ ነበር ተብሏል።

የዐይን እማኙ ጆሹዋ ብራውን ከሟቹ ጋር በአንድ ህንፃ፤ በአራተኛ ፎቅ ላይ ይኖሩ የነበረ ሲሆን ምስክርነቱንም በሰጠበት ወቅት ከእንባ ጋር በተቀላቀለ ሁኔታ ነበር። እንባውንም በቲሸርቱ ሲጠርግ ታይቷል።

ከሟቹ አፓርትመንትም ውስጥ የጥይት ተኩስ መስማቱን አስረድቶ ሁለት ሰዎች በድንገት ሲገናኙ የሚሰማ ድምፅ ከተሰማ በኋላ ተኩሶች ተከትለዋል ብሏል።

አምበር ጉይገር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የአስር አመት ፍርድ ተፈርዶባታል።

አርብ እለት ከሚያልፍ ተሽከርካሪ በተተኮሰበት ጥይትም ምስክርነቱን ከሰጠ ከቀናት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

በመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ሰውነቱ በብዙ ጥይት ተበሳስቶ ወድቆ የተገኘ ሲሆን ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ለማትረፍ አለመቻሉን ነው ቢቢሲ በዘገባው ያመለከተው።

ፖሊስ ጉዳዩ ላይ ምርመራየን አልጨረስኩም ያለ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ግን ከፖሊሷ የፍርድ ሂደት ጋር መገናኘቱን የሚያሳይ ፍንጭ የለም ተብሏል።

በፖሊሷ የተገደለው የቦታም ጂን ቤተሰቦች ጠበቃ ሊ ሜሪት በበኩላቸው የአሜሪካ የፍትህ ሥርዓት ሕይወታቸውን የተቀጠፉትን ጥቁር አሜሪካውያን ሊፋረዳቸው ይገባል ብለዋል።

"ለጂን ቤተሰቦች ፍትህን ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት ከማድረጉ አንፃር እሱም በተመሳሳዩ ፍትህ ይሻል" በማለት ሊ ሜሪት በመግለጫቸው አትተዋል።

የ28 አመቱ ጆሹዋ ብራውን የቀድሞ አትሌትና የሥራ ፈጣሪም በሚል ሁኔታ በአሜሪካ ሚዲያዎች ዘንድ ሲገለፅ ቆይቷል።