አሜሪካ ቱርክ ሶሪያ ላይ ጥቃት እንድትፈፅም ይኹንታዋን እንዳልሰጠች ገለፀች

አሜሪካ ለቱርክ ሰሜናዊ ሶሪያ ላይ ጥቃት እንድትፈፅም 'ይኹንታዋን' እንዳልሰጠች የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማይክ ፖምፒዮ ገለፁ።

ፖምፒዮ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቱርክ የድንበር አካባቢ ጦራቸው እንዲወጣ ማድረጋቸውንም ደግፈዋል።

ይህ እርምጃ ግን በአሜሪካ ባሉ ፓለቲከኞችም ሆነ በሌሎች ወገኖች ዘንድ ድጋፍ አላገኘም።

ቱርክ የአሜሪካ ጦር መውጣቱን ተከትሎ በድንበር አካባቢ በሚገኙና በኩርዶች የሚመራ ጦር ላይ ጥቃት ከፍታለች።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን እንዳሉት፤ ጥቃቱ "ድንበር አካባቢ የሚፈጠር የሽብር ተግባርን መከላከል" ነው።

የቱርክ ጦር ድንበር አካባቢ በከፈተው ጦርነት ኢላማ ያደረገው የኩርድ ወታደሮችን አስወግዶ "ደህንነቱ የተጠበቀ ዞን" መፍጠር ሲሆን ስፍራው ላይ የሶሪያ ስደተኞችም ይኖሩበታል።

የአውሮፓ ሕብረት ግን ይህ ቱርክ ያቀረበችውን ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ መፍጠር የሚል ሀሳብ መሳካቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ተናግሯል።

አክሎም ስደተኞች ሊኖሩበት የሚችሉትና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ መስፈርት ያሟላ ይሆናል የሚለውም ላይ ስጋት እንዳለው አስታውቋል።

ዩ ኬ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየምና ፖላንድ ከተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ጋር በቀጣይ ስለሚወሰዱ ርምጃዎች ለመነጋገር ጥያቄ አቅርበዋል።

የአረብ ሊግም አስቸኳይ ስብሰባ የጠራ ሲሆን፣ ስብሰባው ቅዳሜ ዕለት በካይሮ ይካሄዳል ተብሏል።

በኩርዶች የሚመራው ጦር የቱርክ ጦርን ለመመከት ቃል የገባ ሲሆን፣ ለሚፈፀምበትም ጥቃት ምላሽ መስጠት ጀምሯል።

ኩርዶች አሜሪካ አይ ኤስን ለማሸነፍ ባደረገችው ጦርነት ውስጥ ዋነኛ አጋር የነበሩ ሲሆን በርካታ የአይ ኤስ ተዋጊዎችና ቤተሰቦቻቸውን በእስር ቤትና በመጠለያ ካምፖች በማቆየት እየጠበቁ ይገኛሉ።

ጦርነቱ ከቀጠለ ይህንን ተግባራቸውን ስለመቀጠል አለመቀጠላቸው የታወቀ ነገር የለም።

የአሜሪካ ጦር በሰሜን ሶሪያ የነበሩ ሁለት ከ30 በላይ ምዕራባውያን ገድለዋል በሚል ክስ የቀረበባቸውን የብሪቴይን ዜጎች እንደወሰደ ተናግሯል።

ሁለቱ ሰዎች ኤል ሻፌ ኤልሻኪህ እና አሌክሳንዳ ኮቴይ የሚባሉ ሲሆን 'ዘ ቢትልስ' በሚል ቅፅል ስምም ይታወቁ ነበር።

የቱርክ ጦር ከትናንት ጀምሮ በበርካታ መንደሮች ላይ የአየር ጥቃት ፈፅሟል። በዚህም የተነሳ በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ሠፈራቸውን ጥለው መሸሽ ጀምረዋል።

የኩርድ ጦር ቢያንስ አምስት ንፁኃን ዜጎች በጥቃቱ መሞታቸውን ተናግሮ 25 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል።

የቱርክ መከላከያ ሚኒስትርም ጦሩ ወደ ድንበር ከተሞቹ መግባቱን ገልጿል።

የቱርክ መከላከያ ኃይል በትዊተር ገፁ ላይ 181 "አሸባሪዎች" ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ተናግሯል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)