ድርጅቱ በየ7ሰከንዱ አንዲት ከዕድሜ በታች ሴት ወደትዳር እንደምትገባ አስታወቀ

በአለማችን በየሰባት ሰከንዱ ከ15 አመት በታች ትዳር እንደምትፈፅም አለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ይፋ ያደረገው አዲስ ሪፖርት ጠቁሟል።

ሪፖርቱ እንደ አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ህንድ እና ሶማሊያ ባሉ ሀገራት እድሜያቸው ከ10 አመት የማይበልጡ ህፃናት በእድሜ እጅግ በጣም ከሚበልጧቸው ሰዎች ጋር እንዲጋቡ ይገደዳሉ ይላል።

የህፃናት አድን ድርጅት ያለ እድሜ ጋብቻ በእያንዳንዱ የሴቶች የህይወት ሁደት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።

“ያለ እድሜ ጋብቻ ተፅዕኖ የሴቶችን መሰረታዊ የመማር መብት በመገደብ ይጀምራል፤ የማደግ እና እንደ እኩዮቻቸው የመሆንን መብትም ይጥሳል” ብለዋል የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቶርኒንግ ስቺሚድት።

በለጋ እድሜያቸው ጋብቻ እንዲፈፅሙ የሚደረጉ ህፃናት ባልጠነከረ ሰውነታቸው ለእርግዝና ከመጋለጣቸውም ባሻገር በግብረ ስጋ ግንኙነት በሚተላለፉ እንደ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ባሉ በሽታዎች ተጠቂም ይሆናሉ ነው ያሉት።

ጦርነት፣ ድህነት እና የሰብአዊ ቀውስ ሴቶች በለጋ እድሜያቸው ተገደው ጋብቻ እንዲፈፅሙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቅሰዋል።

ጥናቱ ለሴቶች ትምህርት የማይመቹ ሀገራት፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የታዳጊዎች እርግዝና፣ የእናቶች ሞት እና በፓርላማ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎን በመተንተን የሀገራትን ደረጃ አውጥቷል።

በዚህም መሰረት ቻድ፣ ኒጀር፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ማሊ እና ሶማሊያ ቀዳሚዎቹን ደረጃ ይዘዋል።

የድርጅቱ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ጦርነት ባለባቸው ሀገራት የሚገኙ ህፃናት ተገደው ጋብቻ የመፈፀም እድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው።

በሪፖርቱ የ13 አመቷ የሶሪያ ስደተኛ በሊባኖስ የ20 አመቱን ወጣት ማግባቷ እና በአሁኑ ወቅት የሁለት ወር ነፍሰ ጡር መሆኗ ተጠቅሷል።

“የሰርጉ እለት በጣም ደስ የሚለኝ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን አልሆነም፤ በጣም አሳዛኝ እና በሚያናድዱ ነገሮች የተሞላ ሆኖ ነበር ያለፈው” ብላለች ታዳጊዋ።

“ልጅ እንደምወልድ ሳስብ እድለኝነት ይሰማኛል፤ ይሁን እንጂ እኔ ህፃን ነኝ ሌላ ህፃን የማሳድገው” ስትልም አስተያየቷን ለቢቢሲ ሰጥታለች። 

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ሰብአዊ ቀውሶችም ሴቶች ያለ እድሜያቸው ጋብቻ እንዲፈፅሙ በር ይከፍታሉ።

ለአብነትም በሴራሊዮን ተቀስቅሶ የነበረው የኦቦላ ወረርሽኝ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በማድረጉ 14 ሺህ ህፃናት እንዲያረግዙ ምክንያት መሆኑን አንስቷል።

ዩኒሴፍም በ2030 ያለ እድሜያቸው ጋብቻ የሚፈፅሙ ህፃናት ቁጥር 950 ሚሊየን እንደሚደርስ አስታውቋል፤ ይህም አሁን ካለው 700 ሚሊየን የ250 ሚሊየን ጭማሪ ያለው ነው።

የህፃናት አድን ድርጅት ይህን ሪፖርት ያወጣው ከአለም አቀፉ የሴቶች ቀን ጋር በማያያዝ ነው (ኤፍ.ቢ.ሲ) ።