አሜሪካ በሥነ-ወሊድ ዙሪያ ለሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፏን አቋረጠች

የአሜሪካው ፕሬዚደንት አገሪቷ ከድንበሯ ውጪ በሥነ- ወሊድ ዙሪያ ለሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንዳይደረግ ወሰኑ ፡፡

የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፅንስ ማቋረጥን ሕገወጥ የሚያደርግ የአስፈፃሚ አካል ትዕዛዝን በመፈረማቸው አገሪቷ ከድንበሯ ውጪ በሥነ ወሊድ ዙሪያ ለሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ አቋረጠች፡፡

አዲሱ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ በታዳጊ አገራት ውስጥ በሴቶች መብትና በሥነ ወሊድ ዙሪያ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አጣብቂኝ ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡

አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት በአንዲት አስክርቢቶ እንደዘበት ጫር ያደረጉት ፊርማ፣ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት ዩኤስ አይ ዲ በዓለም ዙሪያ ባሉ ታዳጊ አገሮች በሴቶች መብትና በስነ-ተዋልዶ ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርግ ያግዳል፡፡

በዚህም የተነሳ በስነ ተዋልዶ ማማከርና የህሙማን ቅብብሎሽ ላይ የሚሰሩ እንደ ማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ያሉ ድንበር ዘለል ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ሕጉ ክፉኛ እንደሚጎዳ ነው  የተመለከተው ፡፡

የአሜሪካን መንግስት በዓመት 600 ሚሊየን ዶላር ገደማ ለቤተሰብ ምጣኔና ስነ ተዋልዶ ሥራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ዘ ሀፊንግተን ፖስት የተባለው የሀገሪቷ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

እንደተባበሩትት መንግስታት ድርጅት መረጃ ከሆነ ከሃያ አንድ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ በታዳጊ አገራት የሚሆኑ ሴቶች ንፅሕናውን ባልጠበቀ ሁኔታ ያልታሰበ ፅንስ እንደሚያቋርጡ ይገመታል፡፡

በአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ አስተዳደር ታሪክ ይህ አይነቱ ሕግ ተግባራዊ የሆነው በሮናልድ ሬገን የአስተዳደር ዘመን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1984 ነበር፡፡

አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ይህንኑ ሕግ መልሶ ተግባራዊ አድርጎታል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ተመሳሳይ ሕግ በአገሪቱ ተግባራዊ ቢሆን ደስታቸው እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት መንበራቸው ከመጡ ወዲህ ወደ አስር የሚጠጉ የአስፈፃሚ አካል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን ፤ያሁኑን ትዕዛዝ ጨምሮ በሁለቱ ላይ እንደ ቢ ቢ ሲና ሲ ኤን ኤን ያሉ ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት የፊርማውን ሥነ-ስርዓት በቀጥታ እንዳይዘግቡ አስተጓጉለዋል ነው የተባለው ፡፡