የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለየመን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

በየመን ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህጻናት በምግብ እጥረት  እየተሰቃዩ  በመሆኑን  የአስቸኳይ  ጊዜ  የምግብ  እርዳታ ድጋፍ እንዲደረግ  የዓለም አቀፉ  ማህበረሰብ  ጥሪ አቀረበ ።   

ከየመን   በአጠቃላይ   ከአገሪቱ ህዝብ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ተብሏል፡፡

የየመን መንግስት ደጋፊ የሆነው ሳዑዲ መራሹ ጥምር ኃይል ከየመን አማፅያን ሁቲ ጋር በገጠሙት ፍጥጫ  ምክንያት የየመን  ዜጎች ለከፋ   የምግብ እጥረት  እየተጋለጡ መሆኑን የተለያዩ   ምንጮች  የሚያወጡት  መረጃዎች አመልክቷል  ፡፡

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው መፍትሔ አልባ ጦርነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያደቀቀና ዜጎቿን ላይ የሚያስከትለው  ቀውስነት ተጠናክሮ  መቀጠሉን   በሥፍራው  የሚገኙ   የረድኤት  ሠራተኞች  የሚያቀርቡት  ሪፖርት  ያረጋግጣል ፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የየመን ጉዳይ እጅጉን አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል፡፡ ከአገሪቱ ዜጎች ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች በመሆናቸውን  ለወደፊቱ ትልቅ ስጋት  እንደሚፈጠር አሳስቧል  ፡፡

ከአገሪቱ  25 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አጠቃላይ ህዝብ 19 ሚሊዮን የሚሆኑት የምግብ እርዳታ እየተጠባበቁ ይገኛሉ ይላል- የመንግስታቱ ድርጅት፡፡  ለዚህም ነው  ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን ለየመናውያን በአፋጣኝ እንዲዘረጋ ጥሪ ያቀረበው፡፡

ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑት የመናውያን ደግሞ የምግብ ዋስትናቸው በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ድርጅቱ ያመለከተው፡፡ በመሆኑም አፋጣኝ እርዳታ እየተጠባበቁ ይገኛል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ህፃናት በምግብ እጥረት ህመም እየተሰቃዩ ነው፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የዓለም ዓቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ዳይሬክተር ሮበርት ማርዲኒ ችግሩ በጣም አስከፊና ሰቅጣጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዓለም እጁን በመዘርጋት ለሰብዓዊ ድጋፍ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ዓለም ዓቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ሴቭ ዘ ችልድረን የየመን ግጭት የተረሳና ትኩረት የተነፈገው ቀውስ ይመስላል ብሏል፡፡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱ ህፃናትና ልጆችን ለመደገፍ በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅት በኩል ለየመን እርዳታ ለማድረግ ቃል ከተገባው ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር እስከ አሁን የተለቀቀው 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ለድጋፍ የተገባው ቃል ብዙም እየተተገበረ ላለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ሆስፒታሎችም ከግማሽ በታች ያህሉ ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ የባለሙያ፣ የመድኃኒትና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸው ነው የሚነገረው፡፡

ለየመን የምግብ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮች በጄኔቫ በመሰባሰብ መክረዋል፡፡ ሚኒስትሮቹ ግን ቃል ከመግባት ባለፈ ወደ ተግባር የወረደ ተጨባጭ ውሳኔ ማሳለፍና መተግበር አለባቸው ነው የተባለው፡፡

በየመን ቀውስ 7ሺ600 ንፁኃን ዜጎች ሲሞቱ 42ሺ ያህሉ ደግሞ ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡