ለየመን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል 1ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ተገኘ

በአስቸጋሪ ቀውስ ውስጥ ለምትገኘው የመን የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚውል  የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን  ዶላር  ድጋፍ  መገኘቱን  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ ።

የመን ያጋጠማትን የሰብዓዊ ቀውስ ችግር ለመወጣት  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  ዓለም አቀፍ  ድጋፍን ለማግኘት  ዘመቻውን  ሲያካሄድ መቆየቱን  ይታወቃል ።

ድርጅቱ  ለየመን  ዜጎች  አስፈላጊ የሆነውን  የ2ነጥብ 1 ለማሰባሰብ የተለያዩ  ጥረቶችን ሲያደርግ  የቆየ ሲሆን እስካሁን  1ነጥብ 1 ቢሊዮን  ዶላር ብቻ  ማሰባሰብ ተችሏል ።   ቀረውን  1 ቢሊዮን ዶላር  ለማሰባሰብም   የመንግሥታቱ ድርጅት ጥረቱን  መቀጠሉንም አያይዞ ገልጿል ።  

በየመን ለምግብ እጥረት ከተጋለጡ ከአገሪቱ  ህዝብ  75 በመቶ በላይ የሚሆኑ የመናውያንን ለመርዳት ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ድርጅቱ  በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት በረሀብ አፋፍ ላይ ለሚገኙ የመናውያን ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚስፈልግ በማስታወቅ ነበር ዘመቻውን የጀመረው፡፡

ድርጅቱ እንደገለፀው ከአገሪቱ 25 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ 19 ሚሊዮን የሚሆኑት የምግብ እርዳታ ይጠባበቃሉ፡፡ የምግብ ዋስትናቸው በአስጊ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ ሰባት ሚሊዮን ደርሰዋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ህፃናትም በምግብ እጥረት ህመም መሰቃየት እጣ ፋንታቸው  ሆኗል፡፡

ይህን መሰሉን ችግር እያስተናገደች የምትገኘዋን የመንን ለመታደግ ሁሉም የበኩልን እንዲወጣ  የተለያዩ አካላት መልዕክታቸውን በአፅንዖት አስተላልፈዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም ቀይ መስቀል ማህበርና የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  መንግስታት ለየመን ችግር ጆሮዋቸውን ብቻ ሳይሆን እጃቸውንም እንዲሠነዝሩ  ማሳሰቢያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለየመን የምግብ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ጉባዔ በጄኔቭ ተዘጋጅቷል፡፡ በጉባዔው የተሳተፉት የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮችና ለጋሾች ለጉዳዩ ቃል ከመግባት ያለፈ ተጨባጭ ውሳኔ ማሳለፍ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡   

የመንግስታቱ ድርጅትና ሌሎች በሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ አካላት ለጉባዔተኞቹ‹‹ ድጋፍ የማታደርጉ ከሆነ ባትሰበሰቡ ይሻላል ›› የሚል ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላፈው ነበር፡፡

ጉባዔው ስኬታማ ሊባል በሚችል መልኩ መጠናቀቁን ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡ ከጉባዔው ተሳታፊዎች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊን ዶላር ድጋፍ ተገኝቷል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ጉባዔው ታሪካዊና ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ለአስቸኳይ ድጋፍ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ ቀሪውን አንድ ቢሊዮን ዶላር በቅርቡ ከለጋሾች እንደሚገኝ ድርጅቱ ተስፋ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ለሁለት ዓመት በዘለቀው የየመን ግጭት ከ10 ሺ በላይ ለህልፈተ ህይወት ከ40 ሺ የሚበልጡት ደግሞ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በሳዑዲ መራሹ ጥምር ኃይልና በሁቲ አማፅያን መካከል የሚደረገው ጦርነት ዛሬም በመፍትሄ አልባነት ቀጥሏል፡፡