በአቴንስ አቅራቢያ በተፈጠረው የሰደድ እሳት የ50 ሰዎች ህይዎት ማለፉ ተገለጸ

በግሪኳ መቀመጫ ጥንታዊቷ አቴንስ ከተማ የተነሳው የሰደድ እሳት የ50 ሰዎችን ህይዎት እንደቀጠፈ እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ደግሞ ከባድ ቁስል ማስተናገዳቸው ተገልጸዋል፡፡

በግሪኳ አቴንስ የተነሳው የሰደድ እሳት አሁን ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመሆኑ የበርካታ ዜጎችን ቤት እና መሰረተ ልማት አውድሟል፡፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ደግሞ ከቤት ቀያቸው ተሰደዋል፡፡ በመሆኑ የሀገሪቱ መንግስት ችግሩን ለማርገብ አለምአቀፍ እርዳታን እየጠየቀ ይገኛል፡፡

በግሪክ አቴንስ የተፈጠረውን የሰደድ እሳት ለማስቆም የሀገሪቱ መንግስት የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ቢያሰማራም ሰራተገኞች ግን ስራው አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ነው የገለፁት፡፡ በተፈጠረው የእሳት አደጋ የሟቾች ቁጥር እንደጨመረና ከሟቾቹ መካከል ደግሞ ለጉብኝት የመጡ የሌላ ሀገር ዜጎች እንደሚገኙበት ደግሞ ተመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ቲስፕራስ በአቴንስ ከተማ የተፈጠረውን የሰደድ እሳት ለማስቆም የሚቻላቸውን ማንኛውንም ነገር እንደሚያደርጉና ለዜጎችንም እርዳታ እንደሚያደርጉ ነው የገለፁት::

የሰደድ እሳቱ በአብዛኛው የተስፋፋው በሰሜን ምስራቃዊ የአቴንስ በሚገኘ የመዝናገኛ ቦታዎች ላይ ሲሆን  በአደጋ ከሞቱት መካከል 16ቱ ህፃናት ሲሆኑ 104 የሚሆኑት ደግሞ በከባድ የቆሰሉ እንደሆኑም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቲስፕራሲ አሁን በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የድንገተኛ አደጋ መስጫ ተቋማት አደጋውን ለማስቆም ዝግጁ መሆናቸውን እና በከተማይቱ በተፈጠረው አሰቃቂ ድርጊት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ እንደሚያውጁ ነው ያስታወቁት፡፡

የሀገሪቱ መንግስት አክሎም የተፈጠረውን የሰደድ እሳት ለማብረድ ከጎረቤት የአውሮፓ ሀገራት ተጨማሪ የእሳት ማጥፊያ ሂሊኮፈተር ድጋፍ እንዲደረግለትም እየጠየቀ ነው የሚገኘው፡፡

እስካሁን ድረስ ደግሞ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፖላንድና ፈረንሳይ በግሪክ የተፈጠረውን የሰደድ እሳት ለማብረድ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡

በግሪክ የተፈጠረው የሰደድ እሳት በሀገሪቱ በ2007 እንደፈረንጆች ከተፈጠረው የእሳት አደጋ የአሁኑ አስደንጋጭና አሰቃቂ ተብሎም ተመዝግቧል፡፡ (ቢቢሲ)