በፈረንሳይ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ከ1ሺህ 600 በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

በፈረንሳይ የጣለው ሀይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከ1600 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከተፈናቃዮች መካከል አብዛኞቹ በደቡባዊ ፈረንሳይ መፈናቀላቸው የሀገሪቱ ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረገው የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአንደኛው የበጋ ካምፕ ውስጥ ህጻናትን ለመቆጣጠር እርዳታ በማድረግ ላይ የነበሩ የ70 ዓመት ጀርመናዊ አዛውንት እስካሁን የገባቡት እንዳልታወቀም ነው የተገለጸው፡፡

በአደጋው ክፉኛ የተጠቁት ቦታዎች ጋርድ፣ አርዴች እና ድሮም የሚሰኙት አካባቢዎች ሲሆኑ ዜጎች ከአደጋው ለመታደግ ይቻል ዘንድ ከ400 በላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች፣ ፖሊሶች እና አራት ሄሊኮፕተሮች ተሰማርተዋልም ተብሏል፡፡

የጎርፍ አደጋው የመጣው ደቡባዊ ፈረንሳይና አብዛኛው አውሮፓ ላይ ተከስቶ በነበረው ከባድ ሙቀት ሳቢያ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ የጎርፍ አደጋውን ተከትሎ ስድስት ዲፓርትመንቶች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ቢደረግም አሁንም ድረስ ግን በሀገሪቱ ደቡባዊ ምእራብና ሰሜናዊ ምስራቅ ግዛት ላይ የሚገኙ 17 ሺ የሚጠጉ መኖሪያ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡

በሴንት ጁሊየን ዴ ፔይሮላስ በሚገኝ አንድ የበጋ ካምፕ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ወደ 120 የሚጠጉ ልጆች በጎርፍ አደጋው ሳቢያ ለመፈናቀል ተገደዋል፡፡

አንድ በአቅራቢያው የሚገኝ ሌላ ካምፕ ውስጥ ይኖር የነበረ ሰው ለፈረንሳዩ የቴሌቪዥን መረብ ቢኤፍኤም እንደተናገው ሌላኛው ቅርንጫፍ የሚገኙ ልጆችን ጩኸት መስማት ብንችልም  ልንደርስላቸው ግን አልቻልንም ሲል ተደምጧል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄሮም ታልሮን በከፍተኛ ሁኔታ የሰውነት ሙቀታቸው የቀነሰና አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 10 ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግረዋል፡፡

አርዴች ካምፕ ውስጥ ይኖር የነበረው ሀሪ ኦሌርተን  ከእንቅልፌ የቀሰቀሰኝ ደማቅ ብርሀንና ሀይለኛ ነጎድጓድ ያለው አስፈሪ የመብረቅ ድምጽ ነው ይላል፡፡

ወዲያው መብራት እንደጠፋና የስልክ ኔትወርክም እንደጠፋ የሚናገረው ሀሪ በአቅራቢያ የሚገኘውን የፍሳሽ ማስወገጃ ውኃ ማጠራቀሚያ እጅግ በጣም እየጨመረ መሆኑን ስንረዳ በስፍራው ለመቆየት አዳጋች መሆኑን ተረዳን፤ ይሁንና በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ከተማ እንኳን በመኪና ለመሄድ አስቸጋሪ ነበር፤ዝናቡ እያየለ መጣ፤መንገዶችም ወደ ወንዝነት ለመቀየር አፍታም አልወሰደባቸውም፤ ከአካባቢው ምንም ሳንሆን መውጣታችን ተአምር ነው ሲል ተናግሯል፡፡ (ምንጭ፤ ቢቢሲ)