እስራኤል የ1200 ዓመት ዕድሜ ያለውን መስጂድ በቁፋሮ አገኘች

በእስራኤል ኔጌቭ በረሀ አርኪኦሎጂስቶች 1200 ዓመት ዕድሜ ያለው መስጂድ በቁፋሮ ማግኘታቸው ተነገረ። መስጂዱ ዓለም ላይ ጥንታዊ ከሚባሉት መካከል እንደሚመደብ ተገልጿል።

ወደ ሰባተኛውና ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ዕድሜያቸውን የሚቆጥሩ ቅሪቶች የተገኙት በራሀት ቤድዌን ከተማ ነው።

የእስራኤል ቅርስ ጥበቃ እንዳለው፤ መስጂዱ ሊገኝ የቻለው በአካባቢው ለግንባታ ተብሎ ቁፋሮ በሚካሄድበት ወቅት ነው።

"በአካባቢው በዚህ ክፍለ ዘመን የነበረ እና በመካ እና እየሩሳሌም ከተገኙት መስጂዶች ጋር በእድሜ የሚፎካከር ቅርስ ነው" ሲል የእስራኤሉ የቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ተናግሯል።

ቁፋሮውን የመሩት ባለሙያዎች በበኩላቸው መስጂዱ "በዓለማችን የትኛውም ጥግ ከተገኙት ሁሉ ለየት ያለው ነው" ብለዋል።

የመስጂዱ ምዕመናኖችም የአካባቢው ገበሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን ግምት ተናግረዋል።

መስጂዱ ጣሪያ የሌለው ሲሆን፤ በአራት መአዘን ቅርፅ የታነፀ ነው። ፊቱን ወደ ሙስሊሞች ቅድስቷ ከተማ መካ ያዞረ መስገጃ አለው።

"ይህ የመስጂዱ አቀማመጥ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ሙስሊሞች በዚህ መስጂድ ውስጥ ይሰግዱ እንደነበር ምስክር ነው" ብለዋል የቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ።

የእስልምና ታሪክን እንዳጠኑት ባለሙያዎች ከሆነ ይህ መስጂድ እስልምና ወደ አሁኗ እስራኤል በመጣበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተገነባ ቀደምት መስጂድ ነው ተብሎ ይታመናል።

አክለውም በዚያ ዘመን የነበረውን ሁኔታ የበለጠ ለማወቅ "የዚህ መስጂድ በአካባቢው መገኘት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው" ይላሉ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)