በሩሲያ በሮኬት ፍንዳታ የተከሰተ የጨረር መጠን ከመደበኛው በ16 እጥፍ ይልቃል ተባለ

በሩሲያ ለአምስት ሰው ሞት መንስኤ የሆነው የሮኬት ፍንዳታ በአከባቢ ያለውን የጨረር መጠን ከመደበኛው በ16 እጥፍ ከፍ እንዳደረገው ተገልጿል።

የሩሲያ የኒውክሌር ኤጀንሲ በወደብ ከተማዋ ሴቬሮድቪንስክ የሮኬት ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ በአካባቢው ያለውን የጨረር መጠን በመለካት ይፋ አድርጓል።

180 ሺህ ህዝብ በሚኖርባት ሴቬሮድቪንስክ ከተማ በሚገኙ ስድስት የሙከራ ጣቢያዎች የጨረር መጠኑ የተለካ ሲሆን፥ በዚህም የጨረር መጠኑ ከመደበኛው ከአራት እስከ 16 እጥፍ መጨመሩ ተነግሯል።

መደበኛው የጨረር መጠን በሰዓት 0 ነጥብ 11 ማይክሮ ሲኤቨርት ሲሆን በአንድ ጣቢያ በሰዓት 1 ነጥብ 78 ማይክሮሲኤቨርት መመዝገቡ ተነግሯል።

ይህ መጠን አደጋኛ ከሚባለው ደረጃ በታች መሆኑ የተገለፀ ቢሆንም፥ በሰው ላይ መጠነኛ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል የኒውክሌር ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡

ፍንዳታውን ተከትሎ የጨረር መጠኑ ከመደበኛው ከፍ ያለ እንደነበረ እና ከቆይታ በኋላ ግን ወደ መደበኛ ደረጃ መመለሱን የሴቬሮድቪንስክ ከተማ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ባለስልጣናት ፍንዳታው በተከሰተበት አከባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች አካባውን  ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ ቢሰጡም ሌሎች የሩሲያ ባለስልጣናት ግን ውሳኔውን መቃወማቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡