የአሜሪካ መከላከያ ለትራምፕ አጥር የ3.4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ

የአሜሪካ መከላከያ ኃይል ፔንታጎን በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ለሚገነባው አጥር 3.4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ማርክ እሰፔር 280 ኪሎ ሜትር ለሚረዝመው አጥር ግንባታ የ3.4 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረጉት 127 የሚሆኑ የጦር ኃይሉ ፕሮጀክቶችን በማስቆም ነው ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል በሜክሲኮ እና በአሜሪካ መካከል የግንብ አጥር መገንባት አንዱና አጨቃጫቂው ነበር። ከዛም አልፎ ፕሬዝዳንቱ የአጥሩን ግንባታ ወጪ ሜክሲኮ እንደምትሸፍን ሲናገሩም ከርመዋል።

ሜክሲኮ ለአጥሩ ግንባታ ቤሳቤስቲን እንደማታወጣ ብትናገርም፤ ትራምፕ ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሜክሲኮ እንደምትከፍል ሲያሳውቁ ቆይተዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ ለአጥሩ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ እያፈላለገ ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ሪፑብሊካኖች ግን እስከ 21.5 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ በሚችለው ግንባታ ደስተኛ እንዳልሆኑ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳዮች መምሪያ ዘገባ ያሳያል።

ትራምፕ በበኩላቸው አጥሩ ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደማያወጣ ሲናገሩ ይደመጣል።

የአሜሪካ መከላከያ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገው በ23 የአሜሪካ ግዛቶች እና በ20 ሌሎች አገራት ውስጥ እየተከናወኑ የነበሩ 127 የጦሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለጊዜው እንዲቆሙ በማድረግ መሆኑ ተነግሯል።

ዲሞክራቶች በአሜሪካ ጦር ውሳኔ ደስተኛ አይደሉም። የአሜሪካ ሲቪል ሊበሪቲስ ማኅበር በበኩሉ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአጥር ግንባታው የሚያስፈልጋቸውን ፈንድ ለማግኘት የሚያዙበትን ሕግ በፍርድ ቤት ለማሳገድ ማዘዣ እንደሚያስወጣ ቃል ገብቷል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)