በህንድ ከ120 በላይ ሰዎች በጎርፍ መሞታቸው ተገለጸ

በህንድ ኡታር ፕራዴሽ እና ቢሃር በሚባሉ ግዛቶች በጣለ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ባጋጠመ ጎርፍ ከ120 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

በሁለቱም ግዛቶች የባቡር አገልግሎት፣ ተሽከርካሪዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና የሃይል አቅርቦት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውም ታውቋል።

የኡታር ፕራዴሽ ግዛት አስተዳደር እንዳስታወቀው፤ 93 ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።

በቢሃር ግዛት ደግሞ የሟቾች ቁጥር 29 የደረሰ ሲሆን፣ በግዛቷ ዋና ከተማ ፓትና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት የአደጋ መከላከል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

የየግዛቶቹ ነዋሪዎችም እንደ ጀልባ ባሉ ውሃ ላይ መንሳፈፍ የሚያስችሉ መገልገያዎችን በመጠቀም በተለያዩ ጎዳናዎች ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል። አንዳንዶቹም በውሃ የተዋጡ መኪናዎችንና ንብረቶችን ሲሰበስቡ ታይተዋል።

ከባለፈው አርብ ጀምሮ ከፍተኛ ዝናብ ሲጥልባቸው በነበሩት ግዛቶች የሚገኙ ብዙ የመኖሪያ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በውሃ የተዋጡ ሲሆን፣ ህጻናትና እድሜያቸው የገፉ ዜጎችም ተጋላጭ ሆነዋል።

ግዛቶቹም የጎርፉ መጠን ከአቅማቸው በላይ ስለሆነባቸው የህንድ አየር ሃይል ሄሊኮፍተሮችና አንዳንድ ማሽኖች በመታገዝ ውሃውን የማፋሰስ ስራ እንዲጀምር ጥያቄ አቅርበዋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)