35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአውሮፓ-አፍሪካ ግንኙነት አጀንዳዎች

                                                                 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ

35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአውሮፓ-አፍሪካ ግንኙነት አጀንዳዎች

በደረሰ አማረ

ጥር 24/2014 (ዋልታ) ለ35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ለ40ኛው ለኅብረቱ የሥራ አስፈፃሚዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የአገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ መሆናቸው ይታወቃል።

በዚህ ጉባኤ ውስጥ የአፍሪካ-አውሮፓ ግንኙነትን ለማሻሻል ሊቀርቡ ይገባል የሚባሉ ጭብጦች ምንድን ናቸው የሚለውን ማንሳት ጠቃሚ ነው።

በ35ኛው የመሪዎች ጉባኤ እና በ40ኛው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የሁለቱን ኅብረቶች ግንኙነት በተመለከተ 4 መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊወያይና ሊመክር፤ አቅጣጫም ሊያስቀምጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ።

1) ከአውሮፓ ጋር ምጣኔሃብታዊ እና የፋይናንስ ስምምነትን ማሻሻል

ባለፈው ዓመት የካቲት መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነትን ሚና የተቀበሉትና ቀጣዩ የኅብረቱ የበላይነትን መንበር እንደሚረከቡ የተገመተላቸው የሴኔጋሉ ፕሬዘዳንት ማኪ ሳል ከሰሞኑ የአውሮፓ አፍሪካ ፋውንዴሽን (Europe Africa Foundation) በበይነመረብ ባካሄደው ስብሰባ ላይ አፍሪካ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የምጣኔሃብትና ፋይናንስ ስርዓትን ማሻሻል ዋነኛው እንደሆነ ገልፀው ነበር።

ይህም ሲባል አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት በሚቀጥሉት ዓመታት ከ300 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ዓመታዊ የበጀት ጉድለት ሊያጋጥማት እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር አፍሪካ ከአውሮፓ ጋር የጋራ ምጣኔሃብታዊ እና የፋይናንስ ስምምነት ስልትን መቀየስ እንዳለባት ይመከራል። አፍሪካ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ማለትም እንደ አውሮፓ ኅብረት ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር የሚኖራት ምጣኔሃብታዊና የፋይናንስ አጋርነት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያስገኝላታል። ይህም የአኅጉሪቱን ምጣኔሃብትና የፋይናንስ ስርዓት ለማሻሻል ይረዳል።

2) የአፍሪካ የመሰረተ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች

በነዚህ ጉዳዮች የሁለቱም ኅብረት ግንኙነት መዳበር የአፍሪካ የትምህርት መዋቅሮችን ያስተካክላል፤ ፈጣን እና ጠንካራ የጤና አጀንዳን ለማራመድ ይረዳል፤ እንዲሁም የአፍሪካን የኃይል እና አየር ንብረት ሽግግር ተነሳሽነት ዙሪያ መደጋገፎችን ይፈጥራል የሚል እምነት በብዙ አባል አገራት ዘንድ አለ።

በዋናነት የአፍሪካ ግብርና መር ምጣኔሃብት የተቀረውን ዓለም ከአየር ብክለት ለመታደግ እያገዘ ቢሆንም የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት ፍትሐዊ ድጎማዎችን ባለማግኘታቸው በውጤቱ ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳልሆኑም ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ከዚህ ቀደም አንስተው ነበር።

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት በአንድ ድምፅ የሚናገሩት በመሆኑ የአገራቱን እድገት ደረጃ ያገናዘበ ስልት (ስትራቴጂ) መቅረጽ እንደሚጠበቅ ይነሳል።

3) የተባባሰው የፀጥታ ስጋት የጉባኤው የትኩረት አጀንዳ ይሆናል ተብሎ ይታመናል

በተለይም በአፍሪካ የሳህል አካባቢ፣ ፈረንሳይ ሽብርተኝነትን ለመቅረፍ “እውነተኛ የአፍሪካ-አውሮፓ የጸጥታ አጋርነት” ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ትገልጻለች።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ቡርኪና ፋሶ ባሉ አገራት ውስጥ ቀጥተኛ ወታደራዊና ምጣኔሃብታዊ ሚና አላት። እንዲህ አይነቱ ተሳትፎ በቀጣናው አለመረጋጋትን ከመፍጠሩም ባሻገር የመፈንቅለ መንግሥት እርምጃ ተስተውሏል።

እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰሰፋፋ የመጣው የደኅንነትና ፀጥታ ስጋት ከአንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ተሳትፎ ጋር በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል።

በጥቅሉ በአፍሪካ እየጨመረ በመጣው የሽብርተኝነት ችግር ላይም እንደሚወያዩና ይህንንም እንዴት ማረቅ ያስችላል የሚሉ የመፍትሔ ጉዳዮችን ማመላከት የ35ኛው የመሪዎች ጉባኤ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህም በ2020 አፍሪካን የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አኅጉር ማድረግ የሚል አጀንዳ ይዞ ላልተሳካለት ኅብረት ተጨማሪ የቤት ሥራና በቁጭት መትጋትን የሚጠይቅ ቁልፍ ጉዳይ ለመሆኑ አመላካች ነው።

4) ሕገ ወጥ የሰዎች ፍልሰት

የአፍሪካ ኅብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የሚደረግ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰት ለመዋጋት እና ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል አጀንዳ የመፍጠር ተስፋ እንዳለው መገመት ይቻላል።

በተለይ ለአፍሪካ ወጣቶች ብሩህ የወደፊት ተስፋን የሚሰጡ ሕጋዊ ፍልሰቶችን፤ ማለትም ለትምህርታዊ፤ ለሳይንሳዊ ወይም ለባሕላዊ ዓላማዎች እንዲውሉ ለማድረግ የአፍሪካና አውሮፓ ኅብረት ጠንካራ ግንኙነትን መፍጠር አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ከዚህ ባለፈ ግን 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ወጣት አፍሪካዊያን በአፍሪካ እንዲቆዩና ስደትን ምርጫ እንዳያደርጉ የሚያስችል ተጨማሪ ሃብትን በአኅጉሪቱ መፍጠርና ማቅረብ የሚያስችል አቅጣጫም በአባል አገራቱ ትኩረት ሊያገኝም ይችላል።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ የኔልሰን ማንዴላ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር እንደሆኑት ካርሎስ ሎፕስ አገላለፅ ብዙውን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች በጠቅላላ ጉባኤዎቻቸው ላይ አቋም የሚይዙባቸው ጉዳዮች ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ቢሆንም ለተግባራዊነታቸው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶች ወቅት ተጨባጭ ለወጦች አይስተዋሉም። ይህም ከስብሰባ ባሻገር ተጨበጭ እርምጃን የሚጠይቅ ነው ማለት ነው።

የአፍሪካ ኅብረት 35ኛ የመሪዎች ጉባኤ እና 40ኛ የኅብረቱ የሥራ አስፈፃሚዎች ጉባኤ ከጥር 25 እስከ 29/2014 በዋና መቀመጫው አዲስ አበባ ይካሄዳል።