38 አይነት ምርቶች ኤል ሲ ተከፍቶላቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታገዱ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) 38 አይነት ምርቶች ኤል ሲ (Letter of Credit) ተከፍቶሎላቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በጊዜያዊነት ታገዱ።

ምርቶቹ የብሄራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ጉሙሩክ ኮሚሽን በጥናት ለይቶ ይፋ ያደረጋቸው ናቸው ተብሏል።

በምርቶቹ ላይ እገዳ የተጣለው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሆነው ስላልተገኙና የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ገቢ እቃዎች በቂ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነው ተብሏል።

ምርቶቹ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት እንደሆኑና እገዳው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚቆይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢና ዋና ኢኮኖሚስት ፈቃዱ ድጋፌ ገልጸዋል።

እገዳ የተጣለባቸው መጠጦች (ውስኪ ወይም ቢራ እና ሌሎች አልኮል መጠጦች)፣ ማስቲካ፣ ቸኮሌት፣ ውሃ፣ ሲጋራ፣ ሰው ሰራሽ ማጌጫዎችና መሰል ቁሳቁስ መሆናቸው ተጠቁሟል።

በግለሰቦች ኤል ሲ ተከፍቶባቸው የሚገቡ መኪናዎችንም እገዳው ይመለከታል ነው የተባለው።

ለባንኮች አዲስ ኤል ሲ እንዳይከፍቱ ደብዳቤ እየተሰራጨ እንደሆነ ምክትል ዋና ገዢው ተናግረዋል።

ባንኮች ከሰኞ ጀምሮ እንዲተገብሩም መመሪያ መተላለፉን ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW