4ኛው የኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ ተጀመረ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) 4ኛው ሀገር ዐቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ በሃዋሳ ከተማ መካሄድ ጀመረ።
ከዛሬ ጀምሮ ለ10 ቀናት የሚካሄደው ውድድሩ “የሴቶች እኩል ተሳታፊነት ለሀገራችን ስፖርት ውጤታማነት” በሚል መሪ ቃል ነው።
ውድድሩ ባለፉት ዓመታት በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ በ10 የስፖርት አይነቶች ይካሄዳል ተብሏል።
በዘንድሮ ውድድር ከስምንት ክልሎች እና ከሁለት ከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ ተወዳዳሪዎች በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጼዛ ቴኒስ እና ዳርት ውድድሮች ይሳተፋሉም ነው የተባለው፡፡
በመክፈቻ መርሃግብሩ ላይ የክልል እና የፌዴራል ስፖርት አመራሮች ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት መንግሥት ለሴቶች ተሳትፎ ትኩረት በመስጠት በሴቶች እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችን ለማስቀጠል እና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የተመቻቸውን እድል ክልሎች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ትዝታ ወንድሙ (ከሃዋሳ)