4ኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ በኦሮሚያ ክልል የበላይነት ተጠናቀቀ

ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ) በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ በኦሮሚያ ክልል የበላይነት ተጠናቋል።

ከሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ውድድር ከስድስት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ተሳታፊዎች በ10 የስፖርት አይነቶች ሲወዳደሩ ቆይተዋል።

በውድድሩ መዝጊያ በተደረገ የእግር ኳስ ጨዋታ ኦሮሚያ ክልል ሲዳማ ክልልን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በ4ኛው የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ጨዋታ በኦሊምፒክ ስፖርቶች ውድድር ኦሮሚያ 1ኛ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ 2ኛ ደረጃን ሲይዝ ደቡብ ክልል 3ኛ በመሆን አጠናቋል፡፡

በባህል ስፖርቶች ኦሮሚያ ክልል፣ ሲዳማ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል።

በፖራ ኦሊምፒክ፤ ኦሮሚያ ክልል 1ኛ ፣ ደቡብ ክልል 2ኛ እንዲሁም ሲዳማ ክልል 3ኛ ወጥተዋል።

መስማት በተሳናቸው ስፖርቶች፤ ኦሮሚያ ፣ ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል።

በዊልቸር ቅርጫት ኳስ አዲስ አበባ 1ኛ ሲወጣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልል 2ኛ እና 2ኛ ሆነዋል።

በባህል እና ስፖርት ሚንስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ቸርነት፤ እንደዚህ አይነት ውድድሮች ክልሎች ራሳቸውን የሚፈትሹበት እና የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ በመሆናቸው የተቋረጡ ውድድሮች ለማስጀመር እንሰራለን ብለዋል።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሴቶች አስደናቂ ድል እያስመዘገቡ በመሆኑ የሴቶችን ስፖርት መደገፍ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ ነውም ብለዋል፡፡

በመዝጊያ ሥነ-ሥርአቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች እንዲሁም የክልል እና የከተማ መስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።

ትዝታ ወንድሙ (ከሀዋሳ)