የካቲት 30/2014 (ዋልታ) አራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ዘላቂ የልማት ግቦች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
ጉባኤው ማጠንጠኛውን በኮቪድ 19 ዘመን የወጣቶች የመቋቋም ችሎታ ላይ ያደረገ ሲሆን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ አስጀምረውታል፡፡
በጉባኤው ላይ በአካል ለመሳተፍ ወደ አፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ለመጡ እንዲሁም ባሉበት ሆነው ጉባዔውን በበይነ መረብ እየተሳተፉ ለሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ሚኒስትር ዴኤታዋ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጉባኤው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህ ተሳታፊዎች በአካል የተገኙበት መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ መሻሻሎች መኖራቸው በበጎ የሚወሰድ ቢሆንም በቀጣይ ለሚከሰቱ ተመሳሳይ ፈተናዎች ይበልጥ ንቁ ሆኖ መዘጋጀት እንደሚያስፈግ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ረገድ ወጣቶች ያላቸውን አቅም ተጠቅመው አዳዲስ የመፍትሄ አማራጮችን ለማበልጸግ ቁልፍ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ጠቁመው ይህ ፈተናዎችን ለማሸነፍ የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል፡
በሌላ በኩል ለሦስት ቀናት የሚቆየው ይኸው ጉባኤ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ እንደሚያተኩርና የምንፈልጋትን አፍሪካ ለማግኘት ወጣቶች በአጀንዳ 2030 እና 2063 ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና በግልጽ መለየት ላይ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ዓለም ዐቀፍ እንዲሁም አኅጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በበቂ መጠን አካታች መሆናቸው ላይ ግልጽ ውይይት እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያን እንደ ምሣሌ በማንሳት፣ በ10 ዓመት የልማት እቅድ ላይ ዘላቂ የልማት ግቦች እና አጀንዳ 2063ን ማካተቷን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡