4 ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ በንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ ከ1 ሺሕ 800 በላይ ጥይቶች ተያዙ

ኅዳር 9/2014 (ዋልታ) አራት ኪሎ በሚገኘው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ በንብረት ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጡ ከ1 ሺሕ 800 በላይ ጥይቶች በሕዝብ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ተያዙ፡፡
ጥይቶቹ የተያዙት ረቡዕ ኅዳር 8 ነው፡፡
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለሽብር ተግባሩ የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ጭምር ሲያከማች እና በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን በተላላኪነት እያሰማራ በበርካታ ንፁሃን ላይ አሰቃቂ እልቂት ሲፈፅም እንደቆየ ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሽብር ቡድኑን ሴራ የተረዳው የከተማዋ ነዋሪ በተለያዩ ቦታዎች የሚመለከታቸውን አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እየሰጠ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብሏል፡፡
በቤተ ክህነቱ ግቢ በሚገኝ የንብረት ግምጃ ቤት በሚገኝ የፅህፈት እና የፅዳት እቃዎች ማስቀመጫ ውስጥ በተደረገው ብርበራ የተገኙት 1ሺህ 363 የብሬን እና 493 የሽጉጥ ጥይቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪም 2 የጥይት ማስቀመጫ ሳጥኖች እና 1 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ካዝና ተይዟል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 1 ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራ ሲሆን ሕብረተሰቡ በስልክ፣ በአካል እና ሌሎች የመገናኛ አማራጮችን በመጠቀም እየሰጠ የሚገኘው ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።