ነሐሴ 12/2015 (አዲስ ዋልታ) ጤና ሚኒስቴር ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም የህክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ከፍለው መታከም ለማይችሉ 40 ሺሕ ዜጎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ ነፃ የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
የህክምና አገልግሎቱ በአዲስ አበባ ራስ ኃይሉ ስፖርት አካዳሚ የሚሰጥ ሲሆን ”በጎነት ለጤንነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል ስለመሆኑ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ነጻ ህክምናው በከተማዋ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ለማገዝ ይረዳል።
ከሐምሌ 4/2015 ዓ.ም ጀምሮ ”በጎነት ለጤንነት” በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፍ የክረምት በጎ ፍቃድ ነጻ የህክምና አገልግሎት በማካሄድ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ነው ብለዋል።
እስካሁን 927 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎቸ ነጻ የህክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን ጠቁመው በዚህም ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎች የተሟላ ህክምና እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
ዛሬ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም ህክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተጀመረው ነጻ የህክምና አገልግሎት የዚሁ አካል ሲሆን በሰባት ቀናት ውስጥ ለ40 ሺህ ዜጎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
በከተማዋ ያሉና በተለያየ ምክንያት ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎች እድሉን በመጠቀም ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ ሚኒስትር ደኤታው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚኒሊየም ህክምና ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ በበኩላቸው ነጻ የህክምና አገልግሎቱ በቀላሉ የማይገኙ የህክምና አገልግሎቶችን ጭምር ያካትታል ነው ያሉት።
ለአብነትም የልብ ምርመራና ህክምና፣ የካንሰር፣ የአንገት በላይ፣ የጉበት፣ የአጥንት፣ የደም ግፊትና የስኳር ህመም ህክምናዎች እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በተጨማሪም ለተላላፊ በሽታዎች የመመርመርና ህክምና ይሰጣል ነው ያሉት።
በአገልግሎቱ ከፍለው መታከም የማይችሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችንም ተደራሽ የማድረግ ስራ ይከናወናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለዚህም ሆስፒታሉ አስፈላጊውን የህክምና መሳሪያና ግብዓትን በማሟላት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ጠቁመው የዘርፉ አጋር አካላት እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የህክምና አገልግሎቱ ምርመራን ጨምሮ አስፈላጊው የህክምና እርዳታን እንደሚያካትት ጠቁመው በቀን ከ150 በላይ ሙያተኞች የሚመደቡ ሲሆን በአንድ ቀን ከ4 ሺሕ በላይ ዜጎችን የሚያክሙ ይሆናል።
በማስጀመሪያ መረኃ ግብሩ ላይ ለ60 ህጻናት የአልባሳት ድጋፍ ተደርጓል።