ሚኒስቴሩ ከወጪ ንግድ 4ነጥብ75 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት አቅዷል

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 5/2008 (ዋኢማ) የንግድ ሚኒስቴር ከወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ ፡፡

በሚኒስቴሩ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ በ2009 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከመዓድን ፣ ከግብርናና ከሌሎችም ዘርፎች ወደ ውጭ አገሮች በመላክ 4 ቢሊዮን 75 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅደው እየተንቀሳቀሱ  ናቸው ፡፡

ከግብርና ዘርፍ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፤ ከማኑፋክቸሪንግ 913  ነጥብ 66 ሚሊየን ዶላር ፣የማዕድን 175 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር እንደሚገኝ አመልክተዋል ፡፡

እንደዚሁም ከ1 ሚሊየን በላይ የቁም እንስሳት ወደ ውጭ በመላክ 393 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታሰቡን አቶ አሰፋ ጠቁመዋል ፡፡

ይህንን ለማሳካት ግብርናን የማስፋት ስትራቴጂውን የበለጠ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ በተወዳዳሪ ዋጋ ማቅረብና ጥራትን የማሻሻል ታሳቢ ተደርጎ መወሰዱን አብራርተዋል ፡፡

የተመረተውን ምርትም በተሻለ ወደ ገቢያ እንዲቀርብ የግብይት ስርዓቱን የተሻለና የተሳለጠ የማድረግ የተጀመሩ ዘመናዊ ግብይት ስርዓቶችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

በግብይት ስርዓቶች የማያልፉትን ምርቶችን ደግሞ በአሰራር እየመለሱ የሚሄዱበት አሰራር መኖሩን አስታውቀዋል  ፡፡

ከአምራች ኢንዳስትሪ ጋር በከፍተኛ ዓቅምና ቅልጥፍናን በመስራትና በተለይም የኢንደስትሪ ፓርኮችን በመጠቀም ረገድ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በመሳብ የተሻለ ስራ እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት  ፡፡

በህገወጥ ንግድና ኮንተሮባንድ ላይ ልዩ ቁጥጥር በማድረግ አቅርቦቱ የተሻለ  እንደሚደረግም አቶ አሰፋ አስረድተዋል ፡፡

ብዙ ጊዜ የሚያውኩ የፋይናንስ፣ የሎጅስቲክና የጉሙሩክ አሰራሮችን የበለጠ በመቃኘት የተሻለ ስራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል ፡፡

በየቦታው የተቋቋሙት የልማት ሰራዊቶችን አቀናጅቶ ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት ይበልጥ ይንቀሳቀሳሉ ነው ያሉት ፡፡

የንግድ ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ 2 ቢሊየን 86 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መሆኑ ይታወቃል ዋልታ እንደዘገበው ፡፡