ከቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች 1ነጥብ2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 7/2008 (ዋኢማ)- በአዲሱ በጀት ዓመት ከቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች 1ነጥብ2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

የሚኒስቴሩ የሰብል ምርቶች ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ መሐመድ  ለዋልታ እንዳስታወቁት፤ከቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ምርቶች 98 ሺ 233 ቶን ወደ ውጭ አገሮች ለመላክ አቅደው እየሰሩ ነው ፡፡

ይህም ዓምና ከተላው ምርት ጋር ሲነጻጸር በ26 በመቶ በማሳደግ 1ነጥብ2 ቢሊዮን አሜሪካን ዶላር ማግኘት እንደሚያችል ገልጸዋል ፡፡

የግብይት ሥርዓቱን በጠንካራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት በመምራትና በመደገፍ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ምርቶች፣ የብርዕና አገዳ ሰብሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን እና የባህር ዛፍ አጣና የምርት አቅርቦትን ማሻሻል ላይ ማተኮራቸውን አመልክተዋል፡፡

እንደዚሁም የላኪዎችን ምርት የማዘጋጀት፣ የመደራደር እና የመላክ አቅም በማሳደግ፣ የሎጀስቲክስ አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ፣ የገበያ ማስፋፊያና ትስስር ተግባራትን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አብራርተዋል ፡፡

ዋልታ እንደዘገበው ከ870 ሺ 349 በላይ ቶን በመላክ 977 ሚሊዮን 146 ሺ የአሜሪካን ዶላር እንደተገኘ መገለጹ ይታወሳል ፡፡

በ2007 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ከ783ሺ 724 ቶን ወደ 793,663 ቶን እና በገቢ ከ1ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰዋል ፡፡