የቻይናው የሱፍ ጨርቅ አምራች ኩባንያ በ850 ሚሊየን ዶላር በኢትዮጵያ ፋብሪካዎችን ሊያቋቋም ነው

የቻይናው ግዙፍ የሱፍ ጨርቅ አምራች ኩባንያ ጃሱ ሱሻይን 850 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሚያወጣ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ፋብሪካዎችን ሊያቋቋም ነው።

ኩባንያው በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ግዙፍ የሱፍ ጨርቅ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ከመንግስት ጋር ተፈራርሟል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ እንደተናገሩት፥ በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው በአንድ ወር ውስጥ በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በተሰጠው ቦታ የፋብሪካ ግንባታውን ይጀምራል።

ኢንቨስትመንቱ በሁለት ምዕራፍ የሚከናወን ሲሆን፥ 350 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣው የመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል።

ኩባንያው ከፋብሪካ ግንባታው ጀምሮ ወደ ምርት ሲገባ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን እንደሚፈጥርም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከበግ ፀጉር የሱፍ ጨርቅ በማምረት የሚታወቀው ጃሱ ሱሻይን በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ፥ ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሰ የመጀመሪያው ታዋቂ የሱፍ ጨርቅ አምራች ድርጅት ነው።(ኤፍቢሲ)