የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት የ2016 የሰላም የኖቤል ሽልማትን ወሰዱ

የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ሁዋን ማኑኤል ሳንቶስ የ2016 የሰላም የኖቤል ሽልማትን አሸነፉ።

ፕሬዚዳንት ሳንቶስ በሀገሪቱ ለ52 አመታት የዘለቀውን ብጥብጥ ለማርገብ ከግራ ዘመም አማፅያን ጋር ባደረጉት ጥረት ነው የሰላም የኖቤል ሽልማት የተሰጣቸው።

በኖርዌይ የሚገኘው የኖቤል ኮሚቴ ነው በዛሬው እለት ሽልማቱን ሲያበረክትላቸው ባለፈው ወር ከፋርክ አማፅያን ጋር ያደረጉትን የሰላም ስምምነት አድንቋል።

ይሁን እንጂ ኮሎምቢያውያን በህዝበ ውሳኔ የሰላም ስምምነቱን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኮሎምቢያ የእርስ በርስ ግጭት ከ260 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት የነጠቀ ሲሆን፥ 6 ሚሊየን የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ሀገራቸውን ሳይለቁ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

ፕሬዚዳንት ሳንቶስ ከ376 እጩዎች ቀዳሚ ሆነው በመመረጥ ነው ሽልማቱን ያገኙት።

ለሽልማቱ እጩ ከሆኑት ውስጥ 228ቱ ግለሰቦች ሲሆኑ 148ቱ ድርጅቶች ነበሩ።

ፕሬዚዳንት ሁዋን ማኑኤል ሳንቶስ የተበረከተላቸው የኖቤል ሽልማት የፋርኩን መሪ ሮደሪጎ ሎንዶና (ቲሞቸንኮ) ጋር የሚጋሩት አለመሆኑንም ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)