የአፍሪካ ህብረት ነጻ የንግድ ቀጠና በመመሥረት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ

የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና በመመስረት የወጣቶችን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ አስታውቋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የአፍሪካ ሃገራት የሚኖራቸውን የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር እንደሚያጠናከር የኒጀሩ ፕሬዚዳንት ኢሶፕ መሃመዱ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና መመስረት  የሚለውን ሓሳብ ተቀብለውታል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሰባት የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን እስከአሁን አላደረጉም ፡፡ በመሆኑም በቀጣይ እነዚህን ሀገራት የሚመጥን ስምምነት ለማዘጋጀት ወደ ማዕቀፉ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

የአፍሪካ አህጉር የነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነቱን ያልተቀበሉት  ሰባት የአፍሪካ  ሀገራት እነማን እንደሆኑ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አላነሱም፡፡

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስ እያደረጉት ያለውን የንግድ ልውውጥ 14 በመቶ ብቻ ነው ፡፡ ስለሆነም ይህንን የንግድ ልውውጥ እኤአ በ2021 በእጥፍ ለማሳደግ ህብረቱ የያዘውን እቅድ ወሳኝ ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡