ሳምሰንግ ኩባንያ ከ25 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ አምራች ሳምሰንግ በደቡብ ኮሪያ ከ25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የሚሞሪ ቺፕስ እና የተንቀሳቃሽ ስልክ ማምረቻዎችን ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል፡፡  

ኩባንያው በተለይ የክምችት አቅማቸው ከፍ ያሉ የሚሞሪ ቺፕስ ውጤቶች ተፈላጊነት መጨመሩን ተከትሎ አዳዲስ ማምረቻዎችን ለመገንባት መወሰኑን ነው የገለፀው፡፡

 የዓለማችን ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች አምራች የሆነው ሳምሰንግ  በተለይ በተንቀሳቃሽ ስልክና ከፍተኛ የክምችት አቅም ባላቸው የሚሞሪ ቺፕስ ምርቶቹ በዓለም ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡

መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ሴዑል ያደረገው ሳምሰንግ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የፋብሪካ ማስፋፊያ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

አሁን ታዲያ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን የማስፋፊያ ኢንቨስትመንት ኩባንያው በተፀነሰባት ደቡብ ኮሪያ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው ተንቀሳቃሽ ስልክና ከፍተኛ የክምችት አቅም ያላቸው የሚሞሪ ቺፕሶችን ለማምረት በደቡብ ኮሪያዋ የደቡብ ምዕራብ የኢንዱስትሪ ከተማ ፒዮንግቴክ እና በሌሎችም ከተሞች የ21 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዎን ማለትም ከ25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ለመጀመር ተዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡

ተንታኞች የአሁኑ የሳምሰንግ ውሳኔ እንደ ጃፓኑ ቶሺባ እና ሀይኔክስ ያሉትን የዘርፉ ተቀናቃኞችን በመብለጥ በገቢ ቀዳሚ የሚያደርገው ነው ብለዋል፡፡ 

የአሁኑ የኩባንያው ውሳኔም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃይ ኢን የሀገር ውስጥ አምራቾች የተሻሉ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር የዘርፉን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ማሳሰባቸውን ተከትሎ የተደረሰ ነው ተብሏል፡፡

ሳምሰንግ አሁን እተገብረዋለው ባለው የምርት ማስፋፊያ ዕቅድ መሠረትም ከ440 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድል እኤአ እስከ 2021 ድረስ ብቻ ይፈጠራል ባይ ነው፡፡

በተያዘው ዓመት ለዓለም ገበያ ከቀረበው የሚሞሪ ቺፕስ ሽያጭ 40 ነጥብ 4 በመቶ የቀረበው በኩባንያው ነው፡፡

የሮይተርስ ዘገባ እንዳመለከተው ሳምሰንግ ከዚህ በተጨማሪ ለአዳዲስ የተንቀሳቃሽ ምርቶችና የመብራት የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ለማምረት ከ5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት መድቧል፡

ሳምሰንግ “ጋላክሲ ኤክስ” ተጠቅላይ ስማርት ስልኩን በቅርቡ በበርሊን በሚካሄደው የኤሌክትሮኒክስ የንግድ ትርኢት ላይ ያስተዋውቃል ተብሎ ይጠበቃል።