ሞሮኮ ከአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስትመንትን በመሳብ ቀዳሚ ሀገር መሆኗ ተገለጸ

አፍሪካ ኢንቨስትመንት ኢንዴክስ 2018 በተሰኘዉ አመታዊ ሪፖርት መሰረት ሞሮኮ ከአፍሪካ ሀገራት ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ቀዳሚ ሀገር መሆኗ ተገልጿል፡፡

ግሎባል ኳንተም የተባለዉ አጥኚ ድርጅት 54 የአፍሪካ ሀገራትን ኢንቨስትመንት በመሳብ አቅማቸው ላይ ጥናት አድርጓል፡፡

ጥናት ከተደረገባቸዉ 54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል ሞሮኮ ቀዳሚ ሆናለች፡፡  ሀገሪቱ ቀዳሚ ሀገር እንድትሆን ያስቻላት የኢኮኖሚ እድገት፣ የገንዘብ አቅርቦት፣ አነስተኛ የስጋት ተጋላጭነት፣ የቢዝነስ ከባቢያዊ ሁኔታዎች፣ የስነ ህዝብ አንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ መመዘኛዎች ናቸው፡፡

ሶሻል እና ካፒታል የሚሉት መመዘኛዎችም  የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ብዛት ለማወቅ በመስፈርትነት ውሏል ነው የተባለው፡፡

በኢኮኖሚ ዕድገት መመዘኛ   ኢትዮጵያ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የ8.4 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ቁንጮ ስትሆን፥ አልጄሪያና ሞዛምቢክ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ይከተሏታል፡፡

በገንዘብ አቅርቦት መስፈርት ደግሞ ደቡብ ሱዳን፣ግብፅና አንጎላ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተል ይዘዋል፡፡

በዝቅተኛ ደረጃ የአደጋ ተጋላጭ መስፈርት ደግሞ ቦትስዋና ስትመራ ሞሮኮ  ትከተላለች፡፡  

በሥነ ሕዝብ መስፈርትም ናይጄሪያ ቀዳሚ ስትሆን  ኢትዮጵያና ግብፅ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

በሶሻል ካፒታል መመዘኛ ደግሞ ቱኒዚያ 3.4 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን በመያዝ ቀዳሚ ስትሆን  ሲሸልስና ሞሪሺየስ በበኩላቸው ተከታዮቹን  ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 በአፍሪካ የተመዘገበው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት መጠን 59 ቢሊየን ዶላር ቢሆንም  ይህ መጠን ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣ አኃዝ ስለመሆኑ ሪፖርቱ ያትታል፡፡ 

ከ54ቱ አገራት ውስጥ 15ቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የቻሉ አገራት ናቸዉ ተብለዋል፡፡

በተለይም አንጎላ፣ ግብፅና ናይጄሪያ በውጭ ኢንቨስተሮች ከፍተኛ ፍላጎት የታየባቸው መሆኑን እና በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ  መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡ (ምንጭ፤ ሮይተርስ)