ሚኒስቴሩ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የወረቀት ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የወረቀት ግብዓት /ፐልፕ/ ማምረቻ ፋብሪካ እንደሚገነባ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የቀድሞው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት፥ ድርጅቱ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፋብሪካዎችን እየገነባ ነው።

በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚገነባው የፐልፕ ፋብሪካ በአገሪቱ የሚታየውን የገበያ ክፍተት የሚሞላና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት ያስችላል ተብሏል።

ተቋሙ በግንባታ ላይ ካሉት የስኳርና የኬሚካል ፕሮጀክቶች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።

ከአዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የፐልፕ ማምረቻ ፋብሪካው ሲጠናቀቅ የገበያ ክፍተቱን ለመሙላትና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ የፋብሪካው የግንባታ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በመንግሥትና በባለሃብቶች ትብብር እንደሚሰራ ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው የአዋጪነት ጥናት በመጠናቀቁ በአክሲዮን ሽያጭ ጨረታ የተሳተፉ ባለሃብቶች ምርጫ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው እውን ሲሆን በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በማፋጠን ረገድ አዎንታዊ ሚና አለው ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በመጪው መስከረም እንደሚጀመርም ተገልጿል።

የስኳር ተረፈ ምርት በዋናነት የፐልፕ ግብዓት በመሆኑ የአራቱን የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት ለመጠቀም ፋብሪካው በዚሁ አካባቢ እንዲገነባ መወሰኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።(ኢዜአ)