ምርት ገበያው ቅዳሜ የግብይት ክፍያ አገልግሎት ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ክፍያ አገልግሎት ሥርዓቱን ከመደበኛ የሥራ ቀናት በተጨማሪ ቅዳሜም ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል።

በሚያዚያ ወር 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 45 ሺህ ቶን ምርቶች ማገበያየቱንም ገልጿል።

ምርት ገበያው ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከመደበኛ የስራ ቀናት በተጨማሪ የሚሰጠውን አገልግሎት ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል።

ከዚህ ቀደም አርብ ለተደረጉ ግብይቶች ሰኞ ይፈፀም የነበረውን የክፍያ አገልግሎት እንደሚያስቀርም አስታውቋል፡፡

ይህም የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላትና በግብይት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያስችላል ነው ያለው፡፡

በሌላ በኩል ምርት ገበያው በወር ካገበያያቸው ምርቶች ውስጥ 66 በመቶ የግብይት መጠንና 81 በመቶ ዋጋ በማስመዝገብ ቡና የመጀመሪያውን ደረጃ ቢይዝም የቡና ግብይት መጠን ካለፈው የመጋቢት ወር አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ18 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡

በወሩ ውስጥም 30 ቶን ቡና በሁለት ቢሊዮን ብር መገበያየቱን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ የቀረበው 69 በመቶ በመጠንና 65 በመቶ ዋጋ በማስመዝገብ ከፍተኛውን ቦታ ሲይዝ ስፔሻሊቲ ቡናና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የቀረበ ቡና በሁለተኛና ሶስተኝነት ይከተሉታል፡፡