ዲስትሪክቱ በአንድ ሳምንት ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እንደመነዘረ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መመንዘሩን አስታውቋል።

የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ዓለማየሁ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውጪ አገር ገንዘቦችን በቤታቸው ያስቀመጡ ግለሰቦች ወደ ባንክ አምጥተው እንዲመነዝሩ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ በዲስትሪክቱ ስር በሚገኙ ባንኮች እየተመነዘረ ያለው የዶላር መጠን እየጨመረ ነው።

በዲስትሪክቱ ስር ባሉ 81 ቅርንጫፎች በቀን በአማካኝ ከ110 ሺህ ዶላር በላይ እየተዘረዘረ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል ይመነዘር የነበረው በአማካኝ ከ500 ዶላር ይበልጥ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

”በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ በዲስትሪክቱ ሥር ባሉ ባንኮች 704 ሺህ 301 የአሜሪካ ዶላር ተዘርዝሯል” ብለዋል።

ብዙ የዶላር ክምችት ያላቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ ወደ ባንክ ካመጣን እንጠየቃለን በሚል ስጋት ገንዘባቸውን እየቀናነሱ የሚያመጡበት ሁኔታ መስተዋሉንም ጠቁመዋል ።

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መሰረት ማንኛውም ግለሰብ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የፈለገውን የዶላር መጠን ወደ ሚቀርበው ባንክ በማምጣት ምንጩ ሳይጠየቅ መመንዘር እንደሚችል ገልፀዋል።

በእጃቸው የዶላር ክምችት ያላቸው ሰዎች በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ካልመነዘሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፉ እርምጃዎች ሊጠብቋቸው እንደሚችሉም አቶ ዮሴፍ አመልክተዋል።

ዶላር ይዘው የሚመጡ ደንበኞችም በባንኩ በልዩ ሁኔታ እየተስተናገዱ መሆናቸውንም አቶ ዮሴፍ አስታውቀዋል። (ኢዜአ)