የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማንቸስተር ከተማ የሚያደርግውን በረራ መጀመሩን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እንግሊዝ ማንቸስተር ከተማ አዲስ በረራ በትናንትናው  ዕለት በይፋ ጀመሩን አስታወቀ ።

አየር መንገዱ ወደ ማንቸስተር ከተማ የጀመረው በረራም አየር መንገዱ በእንግሊዝ  ያለውን መዳረሻ ወደ ሁለት ከፍ ያደረገው መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማንቸስተር በረራ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱም ላይ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እና በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር ሱዛና ሞርሄድን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ባደረጉት ንግግር፥ አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1973 ጀምሮ ለ43 ዓመታት ወደ ለንደን ከተማ በረራ ሲያደርግ እንደነበር አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ ወደ ማንቸስተር ከተማ የጀመረው በረራም በብሪታኒያ ሁለተኛ መደረሻው መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በማንቸስተር ከተማ ተጨማሪ በረራ መጀመሩ  ለአየር መንገዱ ደንበኞቹ የበለጠ ቅርብ እንዲሆን   በማድረጉም  ሥራ አስፈጻሚው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የማንቸስተር በረራ መጀመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንግሊዝ በአፍሪካ ካሉት 60 መዳረሻዎቹ ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እንድትችል እንደሚያደርጋትም ገልፀዋል።

አየር መንገዱ ወደ ማንቸስተር በሳምንት 4 በረራዎችን እንደሚያደርግ ያስታወቁት አቶ ተወልደ፥ ይህም ወደ ለንደን ሳምንቱን ሙሉ ከሚያደረገው በረራ ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ ወደ ብሪታኒያ የሚደረገውን ሳምንታዊ በረራ ወደ 11 ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ በሳምንት ወደ አውሮፓ ሀገራት የሚያደርገውን በረራ ወደ 51 ከፍ እንዲል አድርጓል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፥ በቅርቡ ወደ ሩሲያዋ ሞስኮ የሚደረገው በረራ ሲጀመር ደግሞ ወደ 54 ከፍ እንደሚልም አስታውቀዋል።

አየር መንገዱ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ ከሚያደርገው በረራ በተጨማሪ ማርሴ ከተማን ሁለተኛ የፈረንሳይ መዳረሻው ለማድረግ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።