“ድራይቭ ቴክ” የተሰኘው የኮርያ ኩባንያ በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ሊገጣጥም መሆኑ ተገለጸ

"ድራይቭ ቴክ" የተሰኘው የኮርያ ኩባንያ በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል በሚሰሩ መኪኖችን ለመገጣጠም የሚያስችለውን የገበያ ጥናት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የአለም ሀገራት የተለያዩ አማራጮችን እየፈለጉ ነው።

ከዚህ ውስጥ አንዱ ከመኪና የሚወጣውን ጭስ ለማስቀረት በኤሌክትሪክና በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን ማምረት መሆኑ ይገለጻል።

በዚህ ዘርፍ የተሰማራው ‹‹ድራይቭ ቴክ›› የተሰኘው የኮርያ ኩባንያ የኤሌክትሮኒክ ምርቶችን ለማምረት እና በታዳሽ ሃይል የሚሰሩ መኪኖችን መገጣጠም በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ዩን ዮንግ ቼይ ከኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጀማል በከር ጋር መክረዋል።

ኩባንያው ምርቶቹን ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለአውሮፓ ሀገራት ገበያም ጭምር ለማድረስ ፍላጎት ያለው ሲሆን ፕሮጀክቱ ስራ ሲጀምር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግና የሰው ኃይል ልማት ለመፍጠር አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ታምኖበታል። (ምንጭ፡-ኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)