ምርት ገበያ በ2011 በጀት ዓመት የ33.8 ቢሊየን ብር ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2011 በጀት ዓመት 681 ሺ ቶን ምርት በ33 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን አስታውቋል፡፡

ምርት ገበያው በዚህ እየተገባደደ በሚገኘው በጀት ዓመት 673 ሺ 53 ቶን ምርት ለማገበያየት አቅዶ 681 ሺ 845 ቶን ማገበያየት ተችሏል፡፡

በሁሉም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች ለመቀበል ከታቀደው 763 ሺ 151 ቶን ምርት 711 ሺህ 850 ቶን ወይም 93 በመቶ ማስፈጸም መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡   

ከተቋቋመ 11 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን ማገበያየት ችሏል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት አኩሪ አተር እና ሽምብራን ወደ ግብይት እንዲገባ መደረጉን የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኝሁ ነገራ ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቷ የነበረው የአየር ንብረት መዛባት፣ ኮንትሮባንድ እና የቡና ዋጋ መውረድ ምክንያት እቅዱን በተፈለገው ደረጃ ማሳካት አለመቻሉን ነው አቶ ወንድማገኘሁ አክለው ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥለው በጀት ዓመት የኤሌክትሮኒክስ ግብይቶችን ይበልጥ ዘመናዊ ለማድረግ፣ ቀይ ቦሎቄ፣ አረንጓዴ ማሾ፣ ኑግ እና ጥጥን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ በማስገባት 35 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለማገበያየት ማቀዱንም ተገልጿል፡፡

ምርት ገበያው ደረጃውን የጠበቀ መጋዘን መገንባት መጀመሩንም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡