በነሐሴ ወር ከአውሮፕላን ነዳጅ ዉጪ ሌሎች የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት እንቀጥል ተደረገ

ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 30/2011 ዓ.ም ድረስ ከአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ዉጪ ሌሎች የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

መንግስት የሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማስቻል ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎች የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በሐምሌ ወር ሲሸጥበት በነበረው የመሸጫ ዋጋ እንዲቀጥል መወሰኑን ሚኒስቴሩ ለዋልታ በላከው መግለጫ ገልጸዋል፡፡

በዚሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሐምሌ ወር ሲሸጥበት ከነበረው በሊትር 23 ብር ከ31 ሳንቲም በዓለም ወቅታዊ ዋጋ መሰረት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት፤ 1 ብር ከ85 ሳንቲም በመጨመር በሊትር 25 ብር ከ16 ሳንቲም እንዲሸጥ የተወሰነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዓለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ ማስተካከያ ሊደረግ የሚችል መሆኑንም በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ከአንድ ዓመት በላይ ለውጥ ሳይደረግበት በመቆየቱና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በሁሉም የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ላይ ባለፈው ህዳር፣ የካቲት እና ሚያዚያ ወር ላይ መጠነኛ ማስተካከያ መደረጉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው አስታውሷል፡፡