አየር መንገዱ ወደ ሞዛምቢኳ ቤይራ ከተማ በረራ ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞዛምቢኳ ቤይራ ከተማ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

አየር መንገዱ በማዕከላዊ ሞዛምቢክ ወደ ምትገኘው ከተማ በሳምንት ሶስት ቀን የሚያደርገውን በረራ በወሩ መጨረሻ ይጀምራል።

አየር መንገዱ ወደ ትልልቅ እና ዋና ከተሞች ብቻ ሳይሆን ወደ አነስተኛ ከተሞች በረራ በማድረግ ለደንበኞቹ ተጨማሪ የጉዞ እድል እንደሚፈጥርላቸው የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደገብረማርያም ተናግረዋል።

የቤይራ ከተማ በሞዛምቢክ አራተኛዋ ትልቅ ከተማና የንግድ መናኸሪያ መሆኗ ይነገራል።

አየር መንገዱ በሞዛምቢክ በስምንት ከተሞች የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከሞዛምቢክ የሃገር ውስጥ በረራ 99 በመቶ ድርሻ አለው።

የአሁኑ መዳረሻም አውሮፓና አሜሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ደንበኞቹ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችለው ነው ተብሏል።

በአምስት አህጉራት ከ120 በላይ መዳረሻዎች ያሉት አየር መንገዱ፣ በተለይም አፍሪካን ከተቀረው የዓለም ክፍል ጋር በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደሙን ሚና ይወጣል።